በፓርላማ ዲፕሎማሲ ብሔራዊ ጥቅምን በማስጠበቅ ግንኙነትን ያጠናከሩ ስኬታማ ስራዎች ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በፓርላማ ዲፕሎማሲ ብሔራዊ ጥቅምን በማስጠበቅ ግንኙነትን ያጠናከሩ ስኬታማ ስራዎች ተከናውነዋል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2017(ኢዜአ)፦ በፓርላማ ዲፕሎማሲ ባለፉት አራት አመታት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅ ግንኙነትን ያጠናከሩ ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውን አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገሮች ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናካር ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል የፓርላማ ዲፕሎማሲ አንዱ ነው።
በምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባልና የአውሮፓ ህብረት የምዕራብ አውሮፓና የኢትዮጵያ የፓርላማ የወዳጅነት ቡድን ሰብሳቢ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ባለፉት አራት አመታት በፓርላማ ዲፕሎማሲ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአፍሪካ፣ ከአውሮፓ፣ ከምስራቅ አውሮፓ፣ ከእስያ፣ ላቲን አሜሪካና ሌሎች ሀገሮች ጋር የፓርላማ የወዳጅነት ቡድን መስርቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በፓርላማ ቡድኖች አማካኝነት ከአለም ሀገራት ጋር በፖለቲካ፣ በምጣኔ ሃብት፣ በማህበራዊና በጸጥታ ዘርፍ ያላትን ግንኙነት የሚያጠናክሩ ውይይቶችና የልምድ ልውውጦች መደረጋቸውንም ተናግረዋል።
በዚህም የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅና ዓለም አቀፍ ግንኙነትን በማጠናከር በኩል ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
በጎረቤት ሀገሮች የፓርላማ ዲፕሎማሲ ቀጠናዊ ትስስርና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጠናክሩ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውንም አንስተዋል።
እንደ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጻ ኢትዮጵያ ያራመደቻቸው አቋሞች፣ የተካሄዱ ውይይቶችና የተደረጉ ግንኙነቶች ወዳጅነትን የሚያሳድጉ ናቸው።
በኢትዮጵያ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ፣ በቀጣናዊ ጉዳዮች ያላትን ሚና እንዲሁም የተጀመረውን ሪፎርምና የተገኙ ውጤቶችን በማስረዳት በኩል ትልቅ የዲፕሎማሲ ስራ መከናወኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብርት ለውጥን ለመቋቋም በአረንጓዴ አሻራ ያስመዘገበችውን ስኬትና እያከናወነች ያለውን ተግባር በውይይቶችና በዓለም አቀፍ መድረኮች ልምዷን ማካፈሏን አስታውቀዋል።
በምግብ እራስን ለመቻል በግብርና እና የሌማት ትሩፋት እንዲሁም ዘመናዊ ከተሞችን ለመገንባት በኮሪደር ልማት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትም ሀገራት ልምድ የወሰዱባቸው ናቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት አራት አመታት ስኬቶችን ያስመዘገበችበት እንዲሁም በፈተናዎች ውስጥ ያለፈችበት ጊዜ በመሆኑ ለአቻ የፓርላማ አባላት በማስረዳት የፓርላማ ዲፕሎማሲ ትልቅ ሚና ተጫውቷል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ በየትኛውም አካል ላይ ጉዳት እንደማያደርስ፣ ለጎረቤትና ለተፋሰሱ ሀገራት ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው በማስረዳት በኩልም ውጤት መገኘቱን አንስተዋል።
በቀጣይ በሰጥቶ መቀበል መርህ ተለዋዋጭ የሆነውን የዓለም አቀፍ ፖለቲካ ከግምት በማስገባት ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቁ ግንኙነቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።
የሀገርን ጥቅም ማስከበር የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት በመሆኑ የሲቪል ማህበራት፣ መገናኛ ብዙሃንና ግለሰቦች በአንድነት መስራት እንዳለባቸውም አምባሳደሩ አስረድተዋል።