አሰባሳቢ ትርክቶችን በማስረፅና የጋራ በሆኑ ማንነቶች ግንባታ ላይ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
አሰባሳቢ ትርክቶችን በማስረፅና የጋራ በሆኑ ማንነቶች ግንባታ ላይ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል

ሰመራ፤ ሰኔ 5/2017(ኢዜአ)፦ የሚዲያና የኮሙኒኬሸን ባለሙያዎች አሰባሳቢ ትርክቶችን በማስረፅና የጋራ በሆኑ ማንነቶች ግንባታ ላይ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክረው ማስቀጠል እንደሚገባቸው በብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ(ዶ/ር) አስታወቁ።
''የድህረ እውነት ዘመንን በእውቀትና በእውነት” በሚል መሪ ሐሳብ ለአፋር ክልል አመራሮችና የሚዲያና የኮሙኒኬሸን ባለሙያዎች በሰመራ ከተማ ስልጠና እየተሰጠ ነው።
በብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ(ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት ባለፉት ሰባት የለውጥ አመታት አሰባሳቢ ትርክቶችን በማስረፅና የጋራ በሆኑ ማንነቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ሲሰራ ቆይቷል።
በዚህም ህብረ ብሄራዊ ለሆነው የአንድነት ጉዞ የጸና መሰረት ማኖር መቻሉን ተናግረዋል።
በድህረ እውነት ዘመን የጋራ ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን በሚያሳድጉ ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንደሚገባ ጠቁመው በዚህ በኩል የሚዲያና የኮሙኒኬሸን ባለሙያዎች በለውጡ አመታት የተገኙ ውጤቶችን አጠናክረው ማስቀጠል እንደሚገባም አሳስበዋል።
በመድረኩ የተገኙት በብልፅግና ፓርቲ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሀላፊ መሐመድ ሁሴን በበኩላቸው ባለፉት ሰባት ዓመታት ህብረ ብሄራዊ አንድነት መጠናከሩን ገልጸዋል።
የሚዲያና የኮሙኒኬሸን ባለሙያዎች የጋራ ትርክትን ማሰረፅ ላይ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ስልጠናው ለተከታታይ ሶስት ቀናት እንደሚቆይ ተመላክቷል።