የፕሪሚየር ሊጉ 34ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ ይጠናቀቃል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ34ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳሉ። 

በወጣው መርሃ ግብር መሰረት ሲዳማ ቡና ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ይጫወታሉ።

ሲዳማ ቡና በ46 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ማሸነፍ ቡድኑ ከሁለት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ወደ አሸናፊነት እንዲመለስ ያደርገዋል።

ድሬዳዋ ከተማ በ39 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዟል። ማሸነፍ ከወራጅ ቀጠና ለመራቅ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ስንቅ የሚሆነው ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያገኛል።

የ34ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሃ ግብር በወላይታ ድቻ  እና ባህር ዳር ከተማ መካከል ምሽት 12 ሰዓት ላይ ይደረጋል።

ወላይታ ድቻ በ45 ነጥብ 8ኛ ደረጃን ይዟል። ማሸነፍ ለቡድኑ በሊጉ ተከታታይ ድሉን እንዲያስመዘገብ ያስችለዋል።

ባለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ድል ያልቀናው ባህር ዳር ከተማ በ48 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ማሸነፍ ቡድኑን ወደ ድል ጎዳና ይመልሰዋል። 

ሁለቱ መርሃ ግብሮች ሲዳማ ቡና እና ወላይታ ድቻ ሰኔ 1 ቀን 2017 ዓ.ም በነበራቸው የኢትዮጵያ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ምክንያት ወደ ዛሬ መዘዋወራቸውን የሊጉ አክሲዮን ማህበር በመረጃው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም