ኢትዮጵያ እና ቻይና የባለብዙ ወገን ትብብራቸውን ለማጠናከር የጋራ ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 4/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ቻይና በባለብዙ ወገን የትብብር አማራጭ ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጎልበት እንደሚፈልጉ አስታወቁ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) ከቻይና አፍሪካ መድረክ(ፎካክ) የአፈጻጸም ክትትል የሚኒስትሮች ስብሰባ ጎን ለጎን ከቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ጋር ተወያይተዋል።

ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂን ፒንግ ያቀረቡትን ሰላምታ በቻይናው አቻቸው በኩል አድርሰዋል።

የኢትዮጵያና ቻይና በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ስትራቴጂያዊ አጋርነት በማጠናከር እና በ2024 የቤጂንግ የመሪዎች ጉባኤ ፕሬዝዳንት ሺ ጂን ፒንግ ያቀረቧቸውን የፎካክ 10 የአጋርነት ተግባራትን በመተግበር ረገድ ትልቅ ለውጥ መመዝገቡን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።


 

የሁለቱ ሀገራት አጋርነት በደቡብ ደቡብ ትብብር፣ በብሪክስ እና በተመድ እንዲሁም በሌሎች መስኮች ያለው ትብብር ጥሩ ማሳያ እየሆነ መምጣቱን አመልክተዋል።

በቻይና፣ አፍሪካ እና የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት(ዩኒዶ) የሦስትዮሽ አጋርነት በአዲስ አበባ የተከፈተው የኢንዱስትሪ የልህቀት ማዕከል ለአፍሪካ የኢንዱስትሪ ዝመና ከፍተኛ ሚና የሚጫወት እና በአፍሪካ ቻይና ግንኙነት ላይ ጉልህ አሻራ የሚያሳርፍ መሆኑንም ነው ሚኒስትሩ ያነሱት።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በበኩላቸው ከአሁን በፊት የሁለቱ ሀገራት መሪዎች የጋራ መግባባት የደረሱባቸውን መስኮች ወደ ተግባር መለወጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እና ቻይና የደቡብ ደቡብ ትብብር እና የብሪክስ ወሳኝ አባል መሆናቸውን አመልክተዋል።

ዋንግ ዪ ቻይና ኢትዮጵያን ሁነኛ አጋር እና ወዳጅ አድርጋ እንደምትመለከታት በመግለጽ የተሻለ ልማት እንዲመዘገብ አጋርነቱን የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም