የኦዲት ባለድርሻ አካላት ፎረም ተቋማት በሀላፊነት ተልዕኳቸውን እንዲፈጽሙ የሚያግዝ በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የኦዲት ባለድርሻ አካላት ፎረም ተቋማት በሀላፊነት ተልዕኳቸውን እንዲፈጽሙ የሚያግዝ በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 4/2017(ኢዜአ)፦ የኦዲት ባለድርሻ አካላት ፎረም ተቋማት በባለቤትነትና በሃላፊነት ተልዕኳቸውን እንዲፈጽሙ የሚያግዝ በመሆኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሺመቤት ደምሴ(ዶ/ር) ገለጹ።
ቋሚ ኮሚቴ የኦዲት ባለድርሻ አካላት ፎረም የ2017 በጀት አመት አፈፃፀም ላይ ውይይት አካሒዷል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሺመቤት ደምሴ(ዶ/ር) የኦዲት ባለድርሻ አካላት ፎረም እቅድ አፈጻጸም ማጠቃለያ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ ከኦዲት ግኝት ጋር ተያይዞ አስተያየት ከተሰጣቸው ተቋማት ውስጥ ለሶስት ተቋማት የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እንዲሁም ኃላፊዎች የገንዘብ ቅጣት እንዲጣልባቸው መደረጉን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ለሰባት የመንግስት ተቋማት የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እንዲደርሳቸው መደረጉን አንስተው በበጀት ዓመቱ በተከናወኑ የኦዲት ግኝት ተግባራት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻሉን ተናግረዋል።
ይህም የኦዲት ባለድርሻ አካላት ፎረም የተቋማትን አሰራር በመፈተሽ የቁጥጥር ስርዓትን ለማጠናከርና ተጠያቂነትን ለማስፈን አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ፎረሙ ተቋማት በኦዲት ግኝት ዙሪያ ያላቸው ግንዛቤ እንዲጨምርና የበጀት አጠቃቀም ስርዓታቸው ጥንቃቄ የታከለበት እንዲሆን አድርጓል ብለዋል።
የፍትህ ሚኒስትር ሐና አርያስላሴ የኦዲት የጋራ ፎረሙ የሁሉም ተቋማት የጋራ የትኩረት አቅጣጫ ነው ብለዋል።
የጋራ ፎረሙ በቋሚ ኮሚቴው የተገኙ ግኝቶችን በግብዓትነት ለመውሰድና ተጠያቂነትን ለማስፈን ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ነው ያሉት።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) በበኩላቸው በቋሚ ኮሚቴው የቀረበው ሪፖርት በበጀት ዓመቱ በዘርፉ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ይህም በተቋማት መካከል ተናቦ የመስራት ልምድ እንዲዳብርና በኦዲት ግኝት ዙሪያ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት አይነተኛ ሚና አለው ሲሉም ገልጸዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ጥሩማር አባተ በቋሚ ኮሚቴው የሚሰሩ የክዋኔም ሆነ የፋይናንስ ኦዲት ተግባራት ፕላንና ልማት ሚኒስቴር ለሚያከናውነው የተቋማት አፈጻጸም ግምገማ መሰረት የሚሆን ነው ብለዋል።
በተለይም በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ለሚደረገው ''አንድ እቅድ አንድ ሪፖርት አንድ እቅድ አንድ በጀት'' የሚለው አሰራር ተግባራዊ እንዲሆን አስቻይ ሁኔታ ይፈጥራል ነው ያሉት።
በፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሙስና መከላከል ጥናት ዴስክ ኃላፊ ደምሴ ስንሻው በበኩላቸው ፎረሙ የኦዲት ግኝትን መነሻ በማድረግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ተቋማትና የስራ ሃላፊዎች በሪፖርቱ መካተቱ በኦዲት ግኝትም ሆነ ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዞ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በቀላሉ እንደማይታለፉ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ምክትል ዋና ኦዲተር አበራ ታደሰ በበኩላቸው፤ በበጀት ዓመቱ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት የኦዲት ሪፖርቱ እንዲደርስ መደረጉን አመልክተው፤ ያካሔደው የክትትልና የቁጥጥር ስራ የሚበረታታ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ፎረሙ የተቋማት አሰራር ጠንካራና ህጋዊ መስመርን የተከተለ በማድረግ በኩል ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ምክትል ኦዲተሩ አብራርተዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሺመቤት ደምሴ(ዶ/ር) በሰጡት ማጠቃለያ የኦዲት ባለድርሻ አካላት ፎረም የሚወስደው አስተዳደራዊ እርምጃ አላማው ቅጣት ሳይሆን የአሰራር ማሻሻያን ማምጣት ነው ብለዋል።
ይህም ተቋማት በባለቤትነትና በሃላፊነት ተልኳቸውን እንዲፈጽሙ የሚያግዝ በመሆኑ መጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።