በክረምት የመምህራን ስልጠና መርኃ ግብር ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ለቆዩ መምህራን የመውጫ ፈተና ይሰጣል - ትምህርት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በክረምት የመምህራን ስልጠና መርኃ ግብር ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ለቆዩ መምህራን የመውጫ ፈተና ይሰጣል - ትምህርት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 4/2017(ኢዜአ)፦ በክረምት የመምህራን ስልጠና መርኃ ግብር ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ለቆዩ 5ሺህ 521 መምህራን ሰኔ 10 ቀን 2017 የመውጫ ፈተና እንደሚሰጥ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ተፈታኞቹ በፈተና ማዕከላት ሲገኙ ሀገር አቀፉን ብሔራዊ መታወቂያ (ፋይዳ) መያዝ እንደሚጠበቅባቸውም ተገልጿል።
በትምህርት ሚኒስቴር የአካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ ኤባ ሚጀና(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ለመምህራኑ የከፍተኛ ትምህርት መውጫ ፈተና ማክሰኞ ሰኔ 10 ቀን 2017 ዓ.ም በበይነ መረብ ይሰጣል፡፡
በዚህም ትምህርታቸውን በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሲከታተሉ የቆዩ 5ሺህ 521 መምህራን በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በተዘጋጁ 35 የፈተና ማዕከላት እንደሚሰጥም ገልጸዋል፡፡
የመውጫ ፈተናው በ24 የትምህርት መርሃ ግብሮች እንደሚሰጥ የገለጹት መሪ ስራ አስፈጻሚው፤ መምህራኑ ለስድስት ዓመታት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
መምህራኑ ከዲፕሎማ ወደ ዲግሪ የትምህርት ደረጃ የሚያድጉ መሆናቸውን ጠቁመው፤ የመውጫ ፈተናውም ለሁለተኛ ደረጃ መምህርነት ብቁ የሚያደርጋቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ተፈታኞቹ በፈተና ማዕከላት ሲገኙ ሀገር አቀፉን ብሔራዊ መታወቂያ (ፋይዳ) መያዝና በትምህርት ሚኒስቴር የተዘጋጀውን የፈተና ፕሮቶኮል ማክበር እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡