ቀጥታ፡

የኃይማኖት ተቋማት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን፣ አብሮነትና አንድነት እንዲጠናከር የጀመሩትን ጥረት ሊያጠናክሩ ይገባል - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ


ባህርዳር፤ ሰኔ 4/2017(ኢዜአ)፦ የኃይማኖት ተቋማት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን፣ አብሮነትና አንድነት እንዲጠናከር የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ አስገነዘቡ።

3ኛው የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ሀገር አቀፍ የሰላም ጉባኤ ‘‘ኃይማኖቶች ለሰላም፣ ለመከባበርና ለአብሮነት’’ በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በባህርዳር ከተማ በፓናል ውይይት ተካሂዷል።




በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እንድገለጹት የኃይማኖት ተቋማት ግጭትን በማስቆምና ግንኙነት እንዲጠናከር በማድረግ በኩል የማይተካ ሚና አላቸው።

የሰላም ጉባኤው በባህርዳር ከተማ መካሄዱም ለክልሉ ህዝብና መንግስት ልዩ ትርጉም አለው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ስለአብሮነት፣ መቻቻል፣ መከባበርና በመተባበር መምከር አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።




ተቋማቱ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን፣ የህዝቦች አብሮነትና አንድነት እንዲፀና በማድረግ ረገድ የጀመሩትን ሰላምን የመስበክና የማስማማት ሚናቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

እንዲሁም በኃይማኖቶች መካከል አብሮነትና አንድነት እንዲጎለብት ከማድረግ ባለፈ መንግስትና የኃይማኖት ተቋማት ሰላምን ለማዝለቅና አብሮነትን ለማጠናከር በጋራ መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል።




የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጊባኤ ዋና ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው ሰላም ሰርቶ ለመለወጥም ሆነ ለመኖር የህልውናችን እስትንፋስ ነው ብለዋል።

ስለሰላም ሁሌም እንዘምራለን፤ እንናገራለን፤ ለማስተማር እንተጋለን ያሉት ዋና ጸሀፊው የሰላም ጉባኤው አላማም በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ አለመግባባቶች እንዲቆሙና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚደረግ ሁለንተናዊ ጥረት እንደሆነም ተናግረዋል።

በየትኛውም አካባቢ የሚስተዋሉ ግጭቶች ቆመው በሰላማዊ መንገድ ውይይቶችና ንግግሮች እንዲጀመሩ ለማንቃት ያለመ ነው ብለዋል።




ለሰው ልጆችም ሆነ ለፍጥረታት ሰላም አስፈላጊ ነው ያሉት ደግሞ የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ ናቸው።

ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ሰላምን አብዝቶ መስበክ ያስፈልጋል ያሉት ምክትል ከንቲባው ለዚህም የኃይማኖት አባቶች ሰላምን ለማፅናት የማይተካ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።

አሁን የተገኘውን ሰላም በማፅናትና በማዝለቅ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሁሉም ኃይማኖቶች ጥረታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

በመድረኩ በሰላም ላይ ትኩረት ያደረጉ ሁለት ሰነዶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በፓናል ውይይቱ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂዎች፣ ከክልሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ ተዋቂ ግለሰቦች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ሌሎች አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም