ድንቁ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጫዋች ሙሉጌታ ከበደ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ - ኢዜአ አማርኛ
ድንቁ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጫዋች ሙሉጌታ ከበደ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 4/2017 (ኢዜአ)፦ የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂ ሙሉጌታ ከበደ ህይወቱ አልፏል።
ሙሉጌታ ከበደ በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ዛሬ ህይወቱ ማለፉን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
ፌዴሬሽኑ በሙሉጌታ ከበደ ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን በመግለጽ ለቤተሰብ፣ ለወዳጅ ዘመድና ለእግር ኳስ ቤተሰብ መፅናናትን ተመኝቷል።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በጨራሽ አጥቂነቱ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ሙሉጌታ ከበደ በ1959 ዓ.ም በደሴ ከተማ ተወለደ።
በእግር ኳስ ቆይታው ለደሴ ከተማ ከፍተኛ ሁለት፣ ለወሎ ፔፕሲ፣ ለወሎ ምርጥ፣ ለቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ለአዲስ አበባ ምርጥና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫውቷል።
ሁለት ቁጥርን በመልበስ የሚታወቀው አጥቂው ፣ ከ1977 እስከ1989 ዓ.ም ድረስ ለረጅም ዓመታት ለአንድ ክለብ (ለቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ቡድን) በመጫወት ይታወቃል።
ፈጣኑና ደፋሩ አጥቂ የሚል ስያሜ የተሰጠው ሙሉጌታ ተከላካዮችን በማስጨነቅ ግቦችን በቀላሉ የሚያስቆጥርበት መንገድ ከብዙዎች አድናቆት አስችሮታል።
በእግር ኳስ ህይወት ዘመኑ ውስጥ 1977፣ 1978 እና 1986 ዓ.ም የኮከብ ግብ አግቢነትን፣ በ1978 እና 1982 ዓ.ም የኮከብ ተጫዋችነትን ክብር ተጎናፅፏል።
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለረጅም ጊዜያት በቋሚነት በመሰለፍ ከ90 በላይ ጎሎችን አስቆጥሯል። ኢትዮጵያ በምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ (ሴካፋ) አሸናፊ እንድትሆን፣ የጎላ ሚና ተጫውቷል።
ብዙዎች ከመንግስቱ ወርቁ ቀጥሎ የመጣ ድንቅ ተጫዋች መሆኑን ይስማማሉ።
የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ፣ ለሱ ካላቸው ፍቅር የተነሳ፣ የተለያየ ስም እየሰጡ ያሞካሹታል። ወለዬው፣ አሸብር፣ የእግር ኳስ ፈርጥ እና የኳሱ ጌታ ከቅጽል ስሞቹ መካከል ይጠቀሳሉ።
ሙሉጌታ ከበደ ባለ ትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነበር።