ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የመንግስትን የማስፈጸም አቅም ለማሳደግ ሲቪል ሰርቫንቱ ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው

ባህር ዳር፤ ሰኔ 4/2017(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የመንግስትን የማስፈጸም አቅም ለማሳደግ ሲቪል ሰርቫቱን መገንባት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን(ዶ/ር) ገለጹ።

የመንግስት አገልግሎት ሪፎርምን ለመተግበር ለክልል አመራሮች የተዘጋጀ የንቅናቄ መድረክ በባህር ዳር ከተማ ዛሬ ተካሂዷል።

በንቅናቄ መድረኩ የተገኙት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት የመንግስትን የማስፈጸም አቅም ለማሳደግ ተቋማዊ ልህቀትን ማረጋገጥና ብቁና በሙያ ስነ-ምግባሩ የተመሰከረለት ሲቪል ሰርቫንት መገንባት ያስፈልጋል።

ተወዳዳሪና ውጤታማ መሆን የሚቻለው ዘመኑን የሚመጥን በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ ሲቻልና በሙያዊ እውቀቱና ክህሎቱ እንዲሁም በስነ-ምግባሩ የተመሰከረለት ሲቪል ሰርቫንት መፍጠር ሲቻል እንደሆነም አስረድተዋል።




ስለሆነም እንደክልል ከፌደራል የሪፎርም ስራዎች ጋር የተናበቡና ተሻጋሪ የሪፎርም ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ሪፎርሙ በተለይም በስፋት የህዝብ የቅሬታ ምንጭ የሆኑ እንደመሬት፣ ንግድ፣ ማዘጋጃ ቤትና የመሳሰሉትን አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ሌብነትንና ብልሹ አሰራርን ለማስቀረት ያስችላል ብለዋል።

የተቋማት ብቃት የሚለካው በያዙት የሰው ኃይል፣ በአደረጃጀት ጥራትና በአሰራራቸውና በህግ ማዕቀፋቸው እንዲሁም በቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸው እንደሆነ ገልጸው ይህንን ታሳቢ ያደረጉ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።




የክልሉ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ባንችአምላክ ገብረማርያም በበኩላቸው እንደ ሀገር ወደ ተግባር የገባውን የመንግስት አስተዳደርና አገልግሎት ፖሊሲ ሪፎርም ማስፈጸም የሚያስችሉ አዋጆች፣ ፍኖተ ካርታ፣ ስትራቴጂና ልዩ ልዩ ማኑዋሎች ተዘጋጅተው ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል።

ቀልጣፋ፣ ፍትሃዊና ዘመኑን የሚመጥን የመንግስት አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ በእውቀትና በቴክኖሎጂ የበቃ ሲቪል ሰርቫንት መገንባት እንደሚያስፈልግ ገልጸው መሰል ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።

እንደክልል በቴክኖሎጂ የታገዘ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለመዘርጋት ሰፊ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውሰው ለሪፎርሙ ትግበራ ሁሉም ባለድርሻ አካል ኃላፊነቱን መወጣት እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

በመድረኩ የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት የኮሚሽኑ የአደረጃጀት ምዘናና ክፍያ ጥናት ዳይሬክተር አንተነህ ይስማው አገልግሎት አሰጣጡን ዲጂታላይዝ በማድረግ ተገልጋዩ ህብረተሰብ ጊዜና ጉልበቱን ከመቆጠብ በተጨማሪ ፍትሃዊነቱ የተረጋገጠ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው።

የአገልግሎት አሰጣጡ ቀልጣፋና ከኢ-ፍትሃዊነት የጸዳ እንዲሆን ዘመኑን የሚመጥን ቴክኖሎጂ መጠቀምን መሰረት ያደረጉ አሰራሮችን ተደራሽ ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም