ወጣቶች በመዲናዋ በሚከናወኑ የልማት ስራዎች ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶች በመዲናዋ በሚከናወኑ የልማት ስራዎች ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ነው
አዲስ አበባ፤ሰኔ 4/2017(ኢዜአ)፦ወጣቶች በመዲናዋ በሚከናወኑ የልማት ስራዎች፣ በሀገራዊ ፕሮጀክቶችና በዘላቂ ሰላም ግንባታ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባዋ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች ከተውጣጡ ወጣቶች ጋር "የወጣቶች ሚና ለሁለንተናዊ ብልጽግና" በሚል መሪ ሀሳብ ውይይት አካሂደዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ወጣቶች የሀገር ጉልበትና ተስፋ ናቸው ብለዋል።
መንግስት በምጣኔ ሃብት ያደገችና ለዜጎች ምቹ ሀገርን ለመፍጠር በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፥ በዚህ ውስጥ የወጣቶች ሚና ወሳኝ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ወጣቶች የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ከሁኔታዎች ጋር ራሳቸውን በማብቃት ተግተው መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በከተማዋ በሚከናወኑ የልማት ስራዎች፣በሀገራዊ ፕሮጀክቶችና በዘላቂ ሰላም ግንባታ ሂደት ወጣቶች ጉልህ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በከተማዋ በተከናወኑ የልማት ስራዎች በርካታ ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውንም ነው ያነሱት።
የአሁኑ ትውልድ በሀገራዊ ግዙፍ ፕሮጀክቶች፣በአረንጓዴ አሻራ፣ በምግብ ራስን ለመቻል በሚከናወኑ ስራዎችና ሌሎች የልማት ሥራዎች ታሪክ እየሰራ እንደሚገኝ ከንቲባዋ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የምትበለጽገው በተፈጥሮ ሃብቷና ባላት ከፍተኛ ወጣት አምራች የሰው ኃይል መሆኑን ገልጸዋል።
በምጣኔ ሃብት፣በፖለቲካና በማህበራዊ ዘርፎች የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
ወጣቶች በክህሎትና በእውቀት ተወዳዳሪ በመሆን ለኢትዮጵያ ብልፅግና በትጋት መስራት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።