አካዳሚው ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት የስፖርት ዘርፉን ለማሳደግ እያገዘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አካዳሚው ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት የስፖርት ዘርፉን ለማሳደግ እያገዘ ነው

ሀዋሳ፤ ሰኔ 4/2017 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ በመስራቱ የስፖርት ዘርፉን ለማሳደግ እያገዘ መሆኑን የስፖርት ሳይንስ ምሁራን ገለጹ።
የስፖርት ሳይንስ ምሁራኑ እንዳሉት የስፖርት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ውድድሮችንና ስልጠናዎችን በሳይንሳዊ መንገድ መምራት ይገባል።
ለዚህም የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር የጀመረው ቅንጅታዊ ስራም ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።
በባህዳር ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ (ዶ/ር) ደምስ ጋሹ፤ ስፖርት አካዳሚው ባለፉት አመታት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመቀናጀት ከምልመላ እስከ ስልጠና ያሉ ተግባራት ለዘርፉ ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
አካዳሚው ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ለመስራት ስምምነት መፈራረሙን የጠቀሱት ተመራማሪው ይህም በቀጣይ በስፖርት ዘርፉ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህሩ (ዶ/ር) ዘሩ በቀለ በበኩላቸው ለእግር ኳስ ሰልጣኞች የተዘጋጀ ረቂቅ የምልመላና ምዘና አተገባበር የጥናት ሰነድ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
ከ2012 ጀምሮ ጥናት የተደረገበት ሰነዱ የተደራጀና ወጥነት ያለው የምልመላና ምዘና አሰራር ለመዘርጋት የሚያስችልና ቅንጅታዊ አሰራርን የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
አካዳሚው በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በሳይንሳዊ መንገድ ለመፍታት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ክልሎች ጋር በቅንጅት መስራቱ በየአካባቢው ያለውን አቅም ለመለየት እንደሚያስችለውም ተናግረዋል።
የወለጋ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር ደስታ ፍቃዱ፤ አካዳሚው ከትምህርት ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራቱ የሰው ሀብቱን በተገቢው ለመጠቀም ያስችለዋል ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲ ምሁራንም ተግባር ተኮር ትምህርት ላይ በማተኮር የዘርፉን ችግሮች መቅረፍ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ከአካዳሚው ጋር በቅርበት በመስራት በእግር ኳስ፣ በአትሌቲክስና በፓራ ኦሎምፒክ ውጤታማ ተግባር ማከናወናቸውን የገለጹት ደግሞ በአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ አትሌትክስ ማሰልጠኛ ማእከል የአትሌቶች ትምህርትና ስልጠና መሪ ስራ አስፈጻሚ ኢንስትራክተር ገረመው ፈጠነ ናቸው።
በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የጥናት፣ ምርምርና ማማከር አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር (ዶ/ር) አመንሲሳ ከበደ በበኩላቸው አካዳሚው ከሀረማያ፣ ጅማ፣ ሀዋሳ፣ ባህር ዳር፣ መቀሌና አዲሰ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ ለመስራት ስምምነት መፈራረሙን ተናግረዋል።
በቀጣይ በየክልሉ ከአንድ ዩኒቨርሲቲ ጋር ስምምነት የሚያደርግ ሲሆን በስልጠና ማኑዋል ቀረጻ፣ የሰው ሀይልንና ሀብትን በጋራ በመጠቀም፣ የስልጠና ሂደቱን በሳይንሳዊ መንገድ ለመደገፍ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በየአመቱ የሚደረጉ የጥናትና ምርምር ውጤቶችም በዘርፉ ያሉ ችግሮችን እንዲቀርፉ በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በዘንድሮው አመታዊ ጉባኤም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የዘርፉ ምሁራን በጥናት መሳተፋቸውን ገልጸው በእግር ኳስ ላይ ትኩረት መደረጉንም ገልጸዋል።