ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የግጭት መንስኤዎችን በመፍታት ዘላቂ ሰላም እና ልማትን እውን ለማድረግ በውይይት መግባባት ይገባል-ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

ባህር ዳር፤ሰኔ 4/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የግጭት መንስኤዎችን በመፍታት ዘላቂ ሰላም እና ልማትን እውን ለማድረግ በውይይት መግባባት ይገባል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት 3ኛው የሰላም ጉባኤ የተለያዩ አካላት በተገኙበት በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።


 

በጉባኤው መክፈቻ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፤ የኃይማኖት ተቋማት የሀገር ሰላም የህዝብ አንድነት እና ልማት እንዲጠናከር የላቀ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የግጭት መንስኤዎችን በመፍታት ዘላቂ ሰላም እና ልማትን እውን ለማድረግ በውይይት መግባባት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

የኃይማኖት ተቋማት የሰላም ጉባኤ በባህርዳር መካሄዱ ልዩ ትርጉም እንዳለው አንስተው፥ በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉን አቀፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

ሰላምና መቻቻል እንዲጎለብት፣ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን የህዝብና የመንግስት ግንኙነት የሰመረ እንዲሆን የኃይማኖት ተቋማት የጀመሩትን አስተምህሮ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

የሚካሄደው የሰላም ጉባኤም ግብረገብነትና ስብዕናው የተገነባ ትውልድ በቀጣይ እንዲፈጠር የሚኖረው ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነም አስረድተዋል።


 

የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ዋና ፀሃፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ፣ ለግጭት መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን በመነጋገርና በውይይት መፍታት የሀገርን ሰላም ማፅናት የሁሉም ግዴታ መሆኑን አንስተዋል።

በ3ኛው የሃይማኖት ተቋማት የሰላም ጉባኤም በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የታዩ ግጭቶችን በመነጋገርና በመመካከር ለመፍታት የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ለመምከር መሆኑን ገልጸዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የባህርዳር ከተማ አስተደደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ፤ በከተማዋ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የከተማ አስተዳደሩ ሰላምን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን ልማቱ እንዲጠናከር ጥረት እያደረገ መሆኑን አመልክተው፥ የኃይማኖት አባቶችም የተገኘው ሰላም በዘላቂነት እንዲረጋገጥ የድርሻቸውን እንዲወጡም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም