መንግስት ለሰላም ሁሌም በሩ ክፍት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ለሰላም ሁሌም በሩ ክፍት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 3/2017(ኢዜአ)፦ መንግስት በሰላም ዙሪያ ለመወያየት ሁሌም በሩ ክፍት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከመላው ኢትዮጵያ ከተውጣጡ የንግድ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ውይይት አድርገዋል።
የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች የኢትዮጵያ ወቅታዊ የሰላም ሁኔታ እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የተያዙ እቅዶችን አስመልክቶ ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ መንግስት የሚያልመውን ብልጽግና ያለ ሰላም ማሳካት አይችልም ብለዋል።
መንግስት የሰላምን ዋጋ እና የማይተካ ሚና በውል እንደሚገነዘብ አጽንኦት ሰጥተውም አብራርተዋል።
አሁን ላይ ሰላም እየተባለ ያለው ቢዝነስ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኮንትሮባንድ እና ሰውን አግቶ ብር አምጡ የሚሉ አካላት የሰላም እሳቤን ለእኩይ አላማ እያዋሉት ነው ብለዋል።
ህገ ወጥ የንግድ ተግባራት የሰላም ጠንቅ መሆናቸውን ገልጸው መንግስት በጉዳዩ ላይ ጠንካራ እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝና በዚህም ለውጦች መምጣታቸውን አመልክተዋል።
መንግስት ሰላም እንዲመጣ ከሚፈልግ ማንኛውም አካል ጋር በትብብር ለመስራትና ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ዝግጁ ነው ብለዋል።
መንግስት ሁሌም ለሰላም በሩ ክፍት እንደሆነም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት።
የንግዱ ማህበረሰብም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ገንቢ ሚና በመወጣት የበኩሉን ድርሻ ማበርከት እንደሚገባው አስገንዝበዋል።