ፋሲል ከነማ በበረከት ግዛው ጎል ጣፋጭ ሶስት ነጥብ አግኝቷል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 3/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ34ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ፋሲል ከነማ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 1 ለ 0 አሸንፏል።

ማምሻውን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ በረከት ግዛው በ85ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሯል።

ውጤቱን ተከትሎ ፋሲል ከነማ በ41 ነጥብ ደረጃውን ከ14ኛ ወደ 11ኛ ከፍ አድርጓል። ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል።

በሊጉ 9ኛ ድሉን ያሳካው ቡድኑ ከመውረድ ስጋቱ በመጠኑም ቢሆን እፎይታ አግኝቷል።

በሊጉ 12ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ38 ነጥብ ከ13ኛ ደረጃ ወደ 14ኛ ዝቅ ብሏል።

ፋሲል ከነማ ቀሪ የሊግ ጨዋታዎቹን ላለመውረድ እየታገለ ካለው አዳማ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ጋር ያደርጋል።         

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በበኩሉ ቀሪ ጨዋታዎቹን ከመቻል እና ወራጅ ቀጠና ከሚገኘው መቀሌ 70 እንደርታ ጋር ያካሂዳል።  

ቀሪ ጨዋታዎቹ የክለቦቹን በሊጉ የመቆየት እና ያለመቆየት እጣ ፈንታ ይወስናሉ።

ቀን ላይ በተደረገ ጨዋታ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን መቻልን 2 ለ 0 ረቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም