የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ሊጎላ ይገባል

አዲስ አበባ፤ሰኔ 3/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት የፖለቲካ ፓርቲዎች  ተሳትፎ ሊጎላ እንደሚገባ  በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።      

በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ትኩረት ያደረገ  እና የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ያሳተፈ ውይይት ተካሂዷል።


 

አቶ አደም በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ፣እውነታዎችና ኃላፊነቶች ዙሪያ የሚያጠነጥን የውይይት ሰነድ ያቀረቡ ሲሆን ወቅታዊ የሠላም ሁኔታ፣የፖለቲካ ምህዳር እንዲሁም ቀጣናዊ ጉዳዮችን ባቀረቡት ሰነድ ዳስሰዋል።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ተሳትፎን የሚገድቡ ህጎች ላይ ማሻሻያ ከማድረግ ባለፈ ነጻና ገለልተኛ የዲሞክራሲ ተቋማት ለመፍጠር ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል ብለዋል።

አካታች ሀገራዊ ምክክር ሂደት መጀመሩ  ትልቅ ዕድል ይዞ የሚመጣ የፖለቲካ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸው ከዚህ ቀደምም ከታጠቁ ኃይሎች ጋር  የተደረገው የሠላም ሥምምነት ለፖለቲካ ምህዳሩ ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወትም ጠቁመዋል።

እንደ አቶ አደም ገለጻ ጽንፍ የረገጡ እሳቤዎች ፣ነጠላ ትርክትና የተዛቡና ሀሰተኛ መረጃዎች የፖለቲካ ምህዳሩ በሚፈለገው ደረጃ እንዳይሰፋ ከሚያደርጉ ጉዳዮች መካከል መሆኑን አመልክተዋል። 

የፖለቲካ ምህዳሩ ይበልጥ ለማስፋት የጋራ ርብርብ ይጠይቃል ያሉት አቶ አደም ፤ የዲሞክራሲ ተቋማትን ማጠናከር፣ በሀሳብ የበላይነት የሚያምን የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ግንባታን እውን ማድረግ ቀጣይ የትኩረት አቅጫዎች መካከል መሆኑን አመልክተዋል። 

የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ማስከበር ጉዳይ የጋራ አጀንዳ በማድረግ በጋራ መግባባት መንፈስ መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል።  

አካታች ሀገራዊ ምክክሩ ግቡን እንዲመታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ጉልህ ሊሆን እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።


 

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሠለሞን አየለ በበኩላቸው፤ ምክር ቤቱ ለዘላቂ ሠላም መስፈን የበኩሉን ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰዋል።    

አንድነትን ማጠናከር ለችግሮቻችን ዘላቂ እልባት ለማበጀት ሁነኛ መፍትሄ  ነው ያሉት ሰብሳቢው፤ አንድ የሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ልናተኮር ይገባል ብለዋል።


 

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ተወካይ አቶ ሰለሞን ታፈሰ በበኩላቸው ፓርቲዎች ትብብርን በማጠናከር ለሀገር የምናበረክተውን አስተዋጽኦ የበለጠ ልናጎላ  ይገባል ነው ያሉት።   


 

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) ተወካይ ዶክተር ሙሉዓለም ተገኘወርቅ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት የነበሩ የፖለቲካ ስብራቶች ለበርካታ ችግሮች መነሻ መሆኑን ጠቅሰው የፖለቲካ ስብራቶች መጠገን ላይ መረባረብ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።  


 

የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ተወካይ አቶ ለገሰ ላንቃሞ ፤ሠላም የሁሉ ነገር መሰረት ነው ለዘላቂ ሠላም ግንባታ ሥራው  ስኬታማ  እንዲሆን  በጠረጴዛ ዙሪያ የመወያየት ልምዳችን ይበልጥ ሊዳብር ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።   

 

 

                         

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም