ቀጥታ፡

ለቅድመ-ልጅነት ትምህርት ፈሰስ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ለትምህርት ጥራት ጠንካራ መሠረት ይጥላል

አዲስ አበባ፤ሰኔ 3/2017(ኢዜአ)፦በቅድመ-ልጅነት ትምህርት ፈሰስ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ለትምህርት ጥራት ጠንካራ መሠረት ለመጣል የሚያስችል መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂክማ ከይረዲን ገለጹ።

አለም አቀፍ የጨዋታ ቀንን ምክንያት በማድረግ በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት "ብሄራዊ ጨዋታን መሰረት ያደረገ የትምህርት ጉባዔ" ዛሬ ተካሄዷል፡፡


 

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂክማ ከይረዲን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ትምህርት ለሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገትና ለአንድ አገር ብልጽግና የማይተካ ሚና አለው፡፡

አገራት በሰው ልጅ ልማት ላይ የሚያፈሱት ካፒታል በመካከላቸው ለሚፈጠረው የኢኮኖሚ ልዩነት ምክንያት እንደሚሆን ነው የገለጹት፡፡

ይህንን መሰረታዊ ነጥብ የተገነዘበው የኢትዮጵያ መንግስት የትምህርት ተደራሽነትን፣ ጥራትን፣ ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት አከናውኗል ብለዋል።       

በተከናወኑት ተግባራት በአገሪቷ ያሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህጻናት የትምህርት ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ተናግረዋል።   

ይህ እንዳለ ሆኖ የትምህርት ጥራትንና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ጉድለቱን ለመሙላት ቀጣይነት ያለው ትኩረትና ፈጠራ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት አዲስ የትምህርት እና የስልጠና ፖሊሲ ማውጣቱን አስታውሰው፤ ሂደቱ የመንግስትን ጥረት ከማሳደጉ በላይ ተጽዕኖውን ለማጉላት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

በፖሊሲው ከተካተቱ መሰረታዊ ጉዳዮች መካከል ከአምስት እስከ ስድስት ዓመት ላሉ ህጻናት ተደራሽ የተደረገውን ነፃና ሁሉን አቀፍ የትምህርት አሰጣጥ ጠቅሰዋል።  

በተለይ በቅድመ-ልጅነት ትምህርት ላይ ፈሰስ የሚደረግ ኢንቨስትመንት የፖሊሲ ግብዓት ብቻ ሳይሆን ዘላቂ ዕውቀት ለማስጨበጥ የተቀመጠ የረዥም ጊዜ ስትራቴጂ መሰረት መሆኑን አመልክተዋል።

በክፍል ውስጥ በጨዋታ ላይ የተመሰረተ ትምህርት የልጆችን የመማር አቅም ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ የትምህርት ጉባኤው ወቅታዊ እና አስፈላጊ እንደሆነ ጨምረው አሰታውቀዋል።  


 

የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በቅድመ መደበኛ ትምህርት ጨዋታን መሰረት አድርጎ የሚሰጥ ትምህርት ልጆች ራሳቸውን እንዲገልጹና ፈጠራን እንዲያጎለብቱ ያስችላል፡፡ 

በመሆኑም በጨዋታ ላይ ተመስርቶ ለህፃናት የሚሰጠውን ዘመናዊ ትምህርት ከባህላዊው ጋር በማቀናጀት አገር በቀል ዕውቀትን ማስተላለፍ ያስችላል ብለዋል፡፡

በዚህ ረገድ የየአካባቢው ማህበረሰብ አባላት ህፃናትን የሚያስተምሩ ቀዳሚዎቹ መምህራን በመሆናቸው ለስኬቱ በአጋርነት ሊሰሩ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡


 

የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ብርሃነ መስቀል ጠና (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በጨዋታ ላይ የተመሰረተ ትምህርት የልጆችን ፈጠራ፣ ማህበራዊ ክህሎትን፣ ስሜታዊ ደህንነትን እና የመማር ፍቅርን ለማጎልበት የሚያስችል መሆኑን አስታውቀዋል።  

ህጻናት እስከ ስድስት ዓመት ያለው የልጅነት ጊዜያቸው ለአእምሮ እድገት ወሳኝ መሆኑን አንስተው፤ ዘመናዊ ትምህርትን ከባህላዊ ዕውቀት ጋር በማስተሳሰር  በጨዋታ ላይ መሠረት አድርጎ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ  በቀጣይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በጨዋታ ላይ የተመሠረተ ዘመናዊ የትምህርት አሰጣጥን ለማጠናከር በጋራ ይሰራል ብለዋል፡፡ 

የኮተቤ ትምህርት  ዩኒቨርሲቲ ከተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት ጋር በጋራ ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም