የኢኮኖሚ ሪፎርም ግቦችን እውን ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት በጠንካራ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የውጭ ኢንቨስትመንትን መሳብ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 3/2017(ኢዜአ)፦የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ግቦችን እውን ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት በጠንካራ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የውጭ ኢንቨስትመንትን መሳብ እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሀደራ አበራ ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የመሪዎችና ባለሙያዎች ስብሰባ "አዳዲስ መዳረሻዎችን ማሰስ፣ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አንቀሳቃሽ" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ነው።


 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሀደራ አበራ እንዳሉት፤ መድረኩ ለውጭ ጉዳይ ስራዎች መሰረት የሆነውን የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ለማጠናከር ያግዛል፡፡

የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የተፈጠሩ ምቹ የኢንቨስትመንት እድሎችን ከሀገር ውስጥ ባለፈ የውጭ ኢንቨስተሮች እንዲጠቀሙባቸው የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አቅሞችን ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በንግድ ኢንቨስትመንት እና በሌሎች ዘርፎች ለማስተሳሰር ጠንካራ ዲፕሎማሲ መፍጠር ይገባል ብለዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያን ዕምቅ አቅም ለውጭ ባለሀብቶችና ኢንቨስተሮች በሚገባ ማስተዋወቅ የሚያስችል ዘመኑን የዋጀ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ጠንካራ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ አቅም በመፍጠር በንግድ፣ ኢንቨስትመንት እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ስትራቴጂያዊ አጋሮችን ማሰባሰብ ይገባል ብለዋል፡፡

ለሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ስኬታማነት የውጭ ባለሀብቶች እና ኩባንያዎች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን በመግለፅ፣ በዚህም በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የተፈጠሩ ዕድሎችን በሚገባ ማሳወቅ ይገባል ብለዋል።

የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ተሳትፎ ይጠይቃል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሻገር በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ለውጭ ጉዳይ ግንኙነት መሰረት መሆኑን በመጥቀስ፤ ከሀገር በቀል ሪፎርሙ የሚጠበቁ ግቦችን ለማሳካት የተጠናከረ ዲፕሎማሲ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በጸጋዋ ልክ እንድትለማ አቅሟን በማስተዋወቅ ጠንካራ የኢኮኖሚ አጋሮችን መፍጠር ይገባል ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት አማራጮችን በሚገባ ለማስተዋወቅ "የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ስትራቴጂ" ተግባራዊ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

አየርላንድ፣ እስራኤል እና ሌሎች የካሪቢያን ሀገሮች የኢንቨስትመንት አቅማቸውን ማሳደግ የቻሉት የተሻሉ ኢንቨስተሮች በመመልመል መሆኑን ገልጸው፣ ኢትዮጵያም በዚህ ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባታል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተወዳዳሪና ተመራጭ የውጭ ኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗን ጠቅሰው፣ ካላት እምቅ አቅም አንፃር ብዙ መስራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት፡፡

ከዚህም ባለፈ በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት የምታስመዘገብ የኢንቨስተሮችም ፍላጎት በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡


 

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ ቢዝነስ ተኮር ማድረግ የሚያስችል ተሻጋሪ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ዘላቂነት እንዲኖረው የሚያስችል የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መደረጉን ጠቅሰው፣ ለስኬታማነቱ ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በትብብር መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ጥልቅ ምርምሮችን በማካሄድ፣ በአቅም ግንባታና ማማከር የኢትዮጵያን የውጭ ፖሊሲ ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም