በጸጥታ ሃይሉ ጠንካራ የህግ ማስከበር ስራ እና በህዝቡ ትብብርና ተሳትፎ በክልሉ አስተማማኝ ሰላም ማስፈን ተችሏል-ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ

ባህርዳር፤ሰኔ 3/2017 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በጸጥታ ሃይሉ ጠንካራ የህግ ማስከበር ስራ እና በህዝቡ ትብብርና ተሳትፎ በክልሉ አስተማማኝ ሰላም ማስፈን መቻሉን የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ ገለጹ።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ከፌዴራል የጸጥታ ተቋማት ጋር በወቅታዊ የጸጥታና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ እንደገለፁት በክልሉ በተከናወነው ጠንካራ የህግ ማስከበር ስራ አስተማማኝ ሰላምና ጸጥታ ሰፍኗል።

በክልሉ የጸጥታ ችግር በነበረባቸው አካባቢዎች የተከናወኑ ህግ የማስከበር ስራዎች ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበባቸው መሆኑን ገልጸው በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።

በመሆኑም መከላከያ ሠራዊት፣ የክልሉ የጸጥታ ኃይል፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ባከናወኑት ቅንጅታዊ ስራ የላቀ ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል።

በክልሉ አስተማማኝ ሰላምና ደህንነት እንዲረጋገጥ በማድረግ ረገድ የጸጥታ ሃይሉ ጠንካራ ስራ እንዳለ ሆኖ የህዝቡም ጥረትና ትብብር አስደናቂ መሆኑን ኮሚሽነር ዘላለም ገልጸዋል።

ከመንግስትና ከጸጥታ ኃይሉ ጎን በመቆም ሕዝቡ ያሳየው ቁርጠኝነት የሚፈለገው ውጤት መጥቷል ሱሉም ተናግረዋል።

በጥምር ጦሩ እየተከናወነ ያለው የህግ ማስከበር ተግባር በአሁኑ ወቅት በክልሉ በሁሉም አካባቢ አስተማማኝ ሰላም እየተረጋገጠ መምጣቱን ተናግረዋል።

በተወሰኑ ቆላማ የመተላለፊያ ቦታዎች በሚገኙ ቀበሌዎች ፅንፈኛ ኃይሉን የማፅዳት ስራው በተጠናከረ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

የታጠቀው ፅንፈኛ ኃይል እየተካሄደ ያለውን ህግ የማስከበር እርምጃ መቋቋም ባለመቻሉ እርስ በእርስ ከመገዳደል አልፎ መንግስት ያስቀመጠውን የሰላም አማራጭ በመቀበል ቁጥሩ ቀላል የማይባል ኃይል እጁን እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።

ጥቂት የፅንፈኛው ኃይሉ አባላት በቅርብም ሆነ በሩቅ ካሉ ታሪካዊ ጠላቶቻችን የአገልጋይነት ተልዕኮ ተቀብለው በመመለስ የህዝቡን ሰላም ለማወክ ጥረት ቢያደርጉም በሀገር መከላከያ ሰራዊትና በክልሉ ጥምር የፀጥታ ኃይል መንቀሳቀሻ ማጣታቸውን አስገንዝበዋል።

የክልሉ ህዝብም ሰላም የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመረዳት ከፀጥታ ሃይሉ ጎን በመሰለፍ መረጃና ጥቆማ በመስጠት ያልተቆጠበ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

በክልሉ በቀጣይ የሚካሄደው የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሰላም ኮንፈረንስ እና ሌሎችም ወቅታዊና መደበኛ የስራ እንቅስቃሴዎች በሰላም እንዲካሄዱ አስፈላጊው ሁሉ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ስራ መገባቱን አረጋግጠዋል።

በውይይት መድረኩ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ ከፍተኛ መኮንኖች፣ የክልሉ የፖሊስ ሃላፊዎች እና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።


 

በሀገር መከላከያ ሰራዊት የመቶ አንደኛ አየር ወለድ ክፍለጦር ምክትል አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል አየልኝ አስናቀ፤ የክልሉ ህዝብ በፅንፈኛ ኃይሉ እያደረሰ ያለውን ግፍና በደል በቅጡ በመረዳት ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመቆም ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የላቀ ሚና መወጣቱን አንስተዋል።

ፅንፈኛ ኃይሉ መንገድ በመዝጋት፣ በእገታና ግድያ በመፈፀም በህዝቡ ዘንድ ጉዳት ሲያደርስ መቆየቱን አስታውሰው አሁን ላይ ጠንካራ እርምጃ የተወሰደበት መሆኑን ተናግረዋል።


 

የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው በበኩላቸው በተሰሩ ስራዎች የከተማዋ ሰላም እየተረጋገጠና ይበልጥ አስተማማኝ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።

በፅንፈኛ ኃይሉ ላይ በተወሰደ እርምጃ 286 የታጠቀ የፅንፈኛ ኃይሉ አባላትና በዕገታ ወንጀል የተሰማሩ 33 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይም የከተማውን ሰላም ከማስጠበቅ ጎን ለጎን የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና የሚካሄዱ ኮንፈረንሶች፣ ክልልና ሀገር አቀፍ ፈተናዎች በሰላም እንዲጠናቀቁ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም