በጥናትና ምርምር በመታገዝ በስፖርት ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን የሚፈቱ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጥናትና ምርምር በመታገዝ በስፖርት ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን የሚፈቱ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ሀዋሳ፤ ሰኔ 3/2017(ኢዜአ)፦ በቴክኖሎጂ በተደገፈ የጥናትና ምርምር ስራዎች በመታገዝ በስፖርት ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን የሚፈቱ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ አስታወቀ።
አካዳሚው 10ኛውን አመታዊ የስፖርት ሳይንስ ጥናትና ምርምር ጉባኤ በሀዋሳ ከተማ እያካሄደ ነው።
የአካዳሚው ዋና ዳይሬክተር አንበሳው እንየው በወቅቱ እንደገለጹት አካዳሚው በስፖርቱ ዘርፍ ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎችን እያከናወነ ነው።
የጥናትና ምርምር ስራዎቹን በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ የኢትዮጵያ ስፖርት ጆርናል መበልጸጉን ጠቁመው ይህም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚያሳድግ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር እውቅና የተሰጠው ጆርናሉ ለዘርፉ ተመራማሪዎችና ለአካዳሚው የምርምር ስራዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።
ከ2006 ዓም ጀምሮ በአካዳሚው የተከናወኑ ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎች ታትመው ለሚመለከታቸው አካላት መሰራጨታቸውን ገልጸዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም የእግር ኳስ ማሰልጠኛ ሞዴልና የማገገሚያ ማዕከልን ከማጠናከር ጀምሮ በዘርፉ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
በአካዳሚው የጥናትና ምርምር የማማከር አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር አመንሲሳ ከበደ በበኩላቸው በአካዳሚው ስፖርቱን በጥናትና ምርምር የመደገፍ ስራ እያደገ መጥቷል።
በዚህም ለፖሊሲና ለሀገራዊ ትልም ግብዓት የሚሆኑ ውጤቶች እየተገኙ ነው ብለዋል።
የዘንድሮ አመታዊ የምርምር ጉባኤም ስፖርቱን በሳይንሳዊ መንገድ በመምራት ዘርፈ ብዙ ውጤቶችን ለማስመዝገብ በሚያስችሉ ተግባራት ላይ ትኩረት የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።
አካዳሚው በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ለወጣቶች ሳይንሳዊ ስልጠናዎችን በመስጠት ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሚያደርገውን ጥረት ለማጠናከር ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና የዘርፉ ምሁራን ቅንጅታዊ ስራ ይጠናከራል ነው ያሉት።
በመድረኩ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻውን ጨምሮ የስፖርት ምሁራንና ባለሙያች ተሞክሯቸውን ያቀረቡ ሲሆን በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ላይ ያተኮሩ ሰነዶች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግ ተመላክቷል።