በኢትዮጵያ 155ሺህ ስደተኞችን የዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ማድረግ ተችሏል - የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 3/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ 155ሺህ ዓለም አቀፍ ስደተኞችን የዲጂታል መታወቂያ ባለቤት በማድረግ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሐሰን አስታወቁ።

የኢትዮጵያ ስደተኞችን የመቀበል ታሪክ ከህዝቦቿ የእንግዳ ተቀባይነት ባህል የሚመነጭ ነው ብለዋል።

ከጎረቤት ሀገራት የመጡ ስደተኞችም ከተቀባዩ ማህበረሰብ ጋር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብርን በሚያሳድጉ መስኮች በመሳተፍ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነትን እያጎለበተ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ለአብነትም ከጎረቤት ሀገር ደቡብ ሱዳን፣ ከሱዳንና የመሳሰሉት ሀገራት የሚመጡ ስደተኞች የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን ጭምር ልዩ ክብር እንዳላቸው ተናግረዋል።

በቆይታቸውም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚያገኙት ዕውቀትና ክህሎትም ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ኢትዮጵያን እንደሁለተኛ ሀገራችው እንደሚቆጥሯት ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋን በመሸሽ ጎረቤት ሀገራትን ጨምሮ ከ34 ሀገራት በላይ የመጡ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ስደተኞች በኢትዮጵያ እንደሚኖሩ ገልጸዋል።

ከዚህ ውስጥ ከደቡብ ሱዳን፣ ከሱዳን፣ ከኤርትራና ከሱማሊያ የመጡ ስደተኞች ትልቁን ቁጥር በመያዝ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብዙ ቁጥር ያለው ዓለም አቀፍ ስደተኛ የምታስተናግድ ሀገር እንድትሆን እንዳስቻላት አስታውቀዋል።

ስደተኞች የዲጂታል መታዊቂያ ባለቤት እንዲሆኑ ለማድረግም በብሔራዊ መታወቂያ መርሃ ግብር፣ በገንዘብ ሚኒስቴርና በአገልግሎቱ ትብብር እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በአጭር ጊዜ ውስጥም በኢትዮጵያ ከሚኖሩ ስደተኞች መካከል 155ሺህ ስደተኞችን የዲጂታል መታወቂያ ባለቤት በማድረግ በኢትዮጵያ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የዲጂታል መታወቂያው ስደተኞች ከዚህ ቀደም የሚያጋጥማቸውን የአገልግሎት መስተጓጎል በማስቀረት ከፍተኛ ጠቀሜታ እያበረከተላቸው እንደሚገኝ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ስደተኞችን በመቀበል የምታስተናግደበት አሰራር በዓለም አቀፍ ደረጃ ዲፕሎማሲያዊ ትብብርን ማሻሻል ያስቻለ ምስጋና እየተቸራት መሆኑንም አንስተዋል።

ዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶች በሚቀርጿቸው ፕሮጀክቶች ስደተኞችንና ተቀባዩን ማህበረሰብ ተጠቃሚ በሚያደርጉ የልማት ሰራዎች ላይ እንዲውል እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዓለም አቀፍ አሰራር መሰረት ስደተኛ ተቀባይ መንግስታት ተገን በመስጠትና ደኅንነትን እንደሚጠብቁ ጠቅሰው፤ ረጂ ድርጅቶችና ለጋሽ አካላትም መሰረታዊ ድጋፎችን እንዲሚያቀርቡ አስረድተዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች የሚቀርቡ የጤና፣ የምግብና ትምህርትን ጨምሮ ሰብዓዊና መሰረታዊ ድጋፎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያቆሙ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ጫና መፍጠሩን አንስተዋል።

በዚህም ዓለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶችና ለጋሽ አካላት በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች የሚያቀርቡትን የተለያዩ ድጋፎች አጠናክረው እንዲቀጥሉ ዋና ዳይሬክተሯ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም