የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን ከመቻል ጋር ይጫወታል 

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 3/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ34ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። 

ከጨዋታዎቹ ትኩረትን የሳበው ኢትዮጵያ  መድን እና መቻል ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የሚካሂዱት ጨዋታ ነው።

ኢትዮጵያ ቡና ትናንት ነጥብ መጣሉን ተከትሎ የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ሶስት ጨዋታዎች እየቀሩት ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫውን ማንሳቱን አረጋግጧል።

መድን በቀጣዩ ዓመት ኢትዮጵያን ወክሎ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ይሳተፋል።      
                                                                             
መርሃ ግብሩ በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው ቡድን ዋንጫውን ማንሳቱን ማረጋገጡን ተከትሎ የሚያደርገው ጨዋታ ነው። 

ባለፉት ሰባት የሊግ ጨዋታዎች ከድል የራቀው መቻል በ44 ነጥብ 9ኛ ደረጃን ይዟል። 

ምሽት 12 ሰዓት ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ፋሲል ከነማ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ  ነው። 

ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ፋሲል ከነማ በተመሳሳይ 38 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው 13ኛ እና 14ኛ ደረጃን ይዘዋል። 

ማሸነፍ የመውረድ ስጋት ላለባቸው ሁለቱ ክለቦች ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያስገኝላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም