ቀጥታ፡

ተንቀሳቃሽ የመስክ ሆስፒታሉ በኢትዮጵያ ድንገተኛ የጤና አደጋዎች ምላሽ አሰጣጥ አቅምን ያሳድጋል - ዶክተር መቅደስ ዳባ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 2/2017(ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ መንግስት ድጋፍ የተደረገው ተንቀሳቃሽ የመስክ ሆስፒታል በኢትዮጵያ ድንገተኛ የጤና አደጋዎች ምላሽ አሰጣጥ አቅምን እንደሚያሳድግ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።

ድጋፉን በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ኤምባሲ "ዩኬ ሜድ" ከተሰኘ ድርጅት ጋር በተመባበር ያደረጉ ሲሆን 12 ድንኳኖች የያዘ እና የተለያዩ የህክምና አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

በመከላከያ ጎልፍ ክለብ በተካሄደው ርክክብ ሥነ ስርዓት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ በኢትዮጵያ እንግሊዝ አምባሳደር ዳረን ዌልሽ፣ የልማት አጋሮችና ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።


 

ዶክተር መቅደስ ዳባ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ለድንገተኛ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ቡድን የማደራጀቱ ሥራ በትኩረት ሲከናወን ቆይቷል።

250 የድንገተኛ ህክምና የሚሰጡ ባለሙያዎች ሰልጥነው ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመው ይህም እንደሀገር የድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ አሰጣጥ አቅምን የሚያሳድግ ነው ብለዋል።

የእንግሊዝ መንግሥት ተንቀሳቃሽ የፊልድ ሆስፒታል ድጋፍ ማድረጉም ድንገተኛ ጤና አደጋዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

በመስክ ሆስፒታሉ የኢትዮጵያ ድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ሰጪ ባለሙያዎች ልምምድ እንደሚያደርጉ ጠቁመው ይህም ድንገተኛ ጤና አደጋዎች ምላሽ አሰጣጥ እንደሀገር ያለንበት ደረጃ የሚገመገምበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።


 

ከእንግሊዝ የመጡ የጤና ባለሙያዎች ለኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ልምድ እንደሚያካፍሉም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

የእንግሊዝ መንግሥት በጤናው መስክ ድንገተኛ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ላይ የአቅም ግንባታ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ በእናቶችና ህጻናት ጤና አገልግሎት ተደራሽነት ከኢትዮጵያ ጋር በሰፊው እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

የዛሬው ተንቀሳቃሽ የመስክ ሆስፒታል ድጋፍም ጠንካራ ግንኙነቱን የሚያሳይ ነው ያሉት ሚኒስትሯ በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ሥም አመስግነዋል።


 

በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ዳረን ዌልሽ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ድንገተኛ የጤና አደጋዎች ከራስ ባለፈ ሌሎች ሀገራትም በመሳተፍ እያከናወነ ያለው ተግባር የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

የእንግሊዝ መንግሥት በኢትዮጵያ የጤና ስርዓት እንዲጠናከር ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በቅርበት ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው ይሄው ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው ተንቀሳቃሽ ሆስፒታሉ በቀላሉ ከቦታ ቦታ በማዘዋወር አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የነፍስ አድን መሳሪያዎችና የተለያዩ የህክምና ቁሳቁስ የያዘ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አንድ ሆስፒታል ሊይዛቸው የሚገቡ መሳሪያዎች የያዘ በመሆኑ የህክምና አገልግሎትና ተደራሽነትን የሚያሳድግ መሆኑንም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም