ብርቅዬ የዱር እንስሳትና ዕጽዋትን ከህገ ወጥ አደንና ዝውውር የመጠበቅ ተግባርን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል - ሚኒስቴሩ


አዲስ አበባ፤ ሰኔ 2/2017(ኢዜአ)፦ በብሔራዊ ፓርኮች ውስጥ የሚገኙ ብርቅዬ  የዱር እንስሳትና  ዕጽዋትን ከህገ ወጥ አደንና ዝውውር የመጠበቅ ተግባርን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ ገለጹ።

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ሕገ-ወጥ የዱር እንስሳት ዝውውርን ለመቆጣጠር ከዛሬ ጀምሮ ለሚቀጥሉት አምስት ቀናት የሚቆይ የባለድርሻ አካላት ስልጠና በአዲስ አበባ አስጀምሯል።

በስልጠናው የአየር መንገድ ተቆጣጣሪ አካላት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የጉምሩክ ኮሚሽን ተወካዮች፣ ኢንተርፖል፣ የአቬዬሽንና ሌሎች ተቋማት ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ በዚሁ ወቅት፤ ስልጠናው ሕገ-ወጥ የዱር እንስሳትና ዕፅዋት ዝውውርን መቆጣጠር እንዲቻል ግንዛቤ በመፍጠር ጉልህ ፋይዳ እንደሚያበረክት ገልጸዋል።





የፀጥታ እና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት የዱር እንስሳትና ዕፅዋትን ከህገ ወጥ አደንና ዝውውር የመጠበቅ ተግባርን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ጠይቀዋል።

በዚህም ብሔራዊ የዱር እንስሳትና ዕፅዋት ጥበቃ ፓርኮችና የማህበረሰብ ጥብቅ የደን ስፍራዎች ለቱሪዝም ኢኮኖሚያዊ አቅም እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ብርቅዬ የዱር እንስሳት በሚገኙባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎችን በማሳተፍ የአትክልትና ፍራፍሬ እና ሀገር በቀል ዕፅዋት ልማትን ጨምሮ የኢኮ ቱሪዝም ጥበቃ ልማት ላይ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።





የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራ፤ ስልጠናው ሕገ-ወጥ የዱር እንስሳት ዝውውርን ለመቆጣጠርና በትብብር ለመስራት ያለመ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ህገ-ወጥ የዱር እንስሳት ዝውውር ዓይነቱንና ቅርጹን እየቀያየረ እንደሚፈጸም ገልጸዋል።

ስልጠናው ሕገ-ወጥ የዱር እንስሳት አደንና ዝውውር ወንጀሎችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላትን ሚና ለማሳደግ ጉልህ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም