አዋጁ ከተሞችን ከብክለት የጸዱ ምቹና ለኑሮ ተስማሚ ማድረግ የሚያስችል ነው - ባለስልጣኑ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 2/2017(ኢዜአ)የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ ከተሞችን ከብክለት የጸዱ ምቹና ለኑሮ ተስማሚ ማድረግ የሚያስችል መሆኑን የኢፌዴሪ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግንቦት 26 ቀን 2017 . ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ ቁጥር 1383/2017 ሥራ ላይ እንዲውል ማጽደቁ ይታወቃል፡፡

አዋጁ የአየር፣ የውሃና የአፈር ብክለትን ለመቀነስና የዜጎች ጤንነትን ለመጠበቅ የጎላ አበርክቶ ያለው ነው፡፡


 

በባለስልጣኑ የከተማ ቆሻሻ አያያዝና ክትትል ዴስክ ኃላፊ ዋሲሁን ዓለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የከተሜነት መስፋፋትን ተከተሎ የህዝብ ቁጥር በመጨመሩ የአኗኗር ዘይቤው ተለውጧል፡፡

በዚህም ነባሩ አዋጅ ቁጥር 513/1999 የከተሞችን የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስርዓት መልክ ለማስያዝ ውስንነቶች ስላሉበት በአዋጅ ቁጥር 1383/2017 እንዲተካ ተደርጓል ብለዋል።

ከተሞች ጽዱና ለኑሮ ተስማሚ እንዲሆኑ የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስርዓት ምን መምሰል አለበት የሚለውን ለመቆጣጠርና ለመከታተል ይቸገሩ እንደነበር ገልጸዋል።

ነባሩ አዋጅ ግለሰቦች፣ ማህበራትና ድርጅቶች  የሚያመነጩትን ቆሻሻ መቀነስ አልያም በአግባቡ ማስወገድ ወይም በድጋሚ ጥቅም ላይ ማዋል የሚችሉበትን መንገድ በግልጽ ያስቀመጠ አልነበረም ብለዋል፡፡

በቅርቡ የጸደቀው አዋጅ ግለሰቦች ከመኖሪያ ቤታቸው 20 ሜትር፣ አገልግሎት ሰጭ ተቋማትና የንግድ ድርጅቶች ደግሞ 50 ሜትር ዙሪያ እንዲያጸዱ ያስገድዳል ነው ያሉት፡፡

ያመነጩትን ቆሻሻ በዘፈቀደ መጣል ወይም ማስወገድ አይቻልም ያሉት ኃላፊው፤ ከተማ አስተዳደሩ በሚለያቸው ስፍራዎች አልያም ፈቃድ ለተሰጣቸው ቆሻሻ ሰብሳቢዎች ማስረከብ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡


 

በባለስልጣኑ የአካባቢ ህጎችና ደረጃዎች ዴስክ ኃላፊ ወንደሰን ታደሰ በኢትዮጵያ የፕላስቲክ ምርቶችን የመጠቀም ባህል በእጅጉ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

የተሻሻለው አዋጅ በተለየ ሁኔታ እንዳይመረቱና ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ክልከላ ያደረገው ለአንድ ጊዜ ብቻ አገልግሎት ላይ በሚውሉ የፕላስቲክ ከረጢቶች በተለምዶ "ፔስታል" በሚባሉት ምርቶች ላይ ብቻ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በፕላስቲክ ከረጢት ላይ የተለየ ክልከላ የተደረገው በአካባቢ ብክለትና በማህበረሰብ ጤና ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት ታሳቢ በማድረግ ነው ብለዋል፡፡

በነባሩ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ ስፋታቸው 0 ነጥብ 03 ሚሊ ሜትር በታች የሆኑ የፕላስቲክ ከረጢቶችን ማምረት ይቻል እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በባለስልጣኑ የከተማ ቆሻሻ አያያዝና ክትትል ዴስክ ኃላፊ ዋሲሁን ዓለሙ እንዳብራሩት ፌስታሎቹ በቀላሉ የሚመረቱ በመሆናቸው ማን የት እንዳመረታቸው ለመቆጣጠርና ርምጃ ለመውሰድ አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡

በዚህም 11 በመቶ የማይበልጠው የፕላስቲክ አጠቃቀም በአሁኑ ወቅት 400 በመቶ በላይ ዕድገት ማሳየቱን ጠቅሰው፤ የፕላስቲክ ከረጢቶች ሙሉ በሙሉ እንዳይመረቱ ክልከላ ማድረግ የተሻለ አማራጭ ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡

የፕላስቲክ ከረጢቶችን ማምረትና መጠቀም አዋጁ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራት ተፈፃሚ እንደማይሆን የገለጹት ደግሞ የአካባቢ ህጎችና ደረጃዎች ዴስክ ኃላፊ ወንደሰን ታደሰ ናቸው፡፡


 

በቀጣዩ ስድስት ወራት ሙሉ ክልከላ የተደረገባቸው እንዲሁም በከፊል ሊፈቀዱ የሚችሉት የፕላስቲክ አይነቶች የትኞቹ እንደሆኑ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ይከናወናል ብለዋል፡፡

ይህም በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾችና ከውጭ የሚያስገቡ ነጋዴዎች ወደ ሌላ ዘርፍ ሽግግር የሚያደርጉበት ጊዜ እንዲኖራቸው ታሳቢ ተደርጎ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከስድስት ወር በኋላ በደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ ቁጥር 1383/2017 የተቀመጡ ግዴታዎች ተግባራዊ እንደሚደረጉም አረጋግጠዋል።

በባለስልጣኑ የከተማ ቆሻሻ አያያዝና ክትትል ዴስክ ኃላፊ ዋሲሁን ዓለሙ፤ የከተማ አስተዳደሮች ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ተቋማት ተዘዋውረው ቆሻሻ መሰብሰብ ለሚችሉ ማህበራት ፈቃድ እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የከተማ አስተዳደሮች ቆሻሻ ለመሰብሰብ የሚጠበቅበትን ክፍያ መክፈሉን፣ ቆሻሻውን ፈቃድ ለተሰጣቸው አካላት ማስረከቡን ይከታተላል፤ ይቆጣጠራል ብለዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ በአዋጁ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን አልፈው የተገኙ አካላት የከተማ አስተዳደሮች በሚያወጡት መመሪያ መሰረት በአስተዳደራዊ ህጎች በወንጀል ተጠያቂ ይሆናሉ ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም