ሰባተኛውን ሀገራዊ ምርጫ በቴክኖሎጂ ማከናወን የሚያስችል መተግበሪያ ማበልጸግ ተችሏል - የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 2/2017(ኢዜአ)የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ የዕጩዎችንና የመራጮችን ምዝገባ በቴክኖሎጂ የታገዘ ማድረግ የሚያስችል መተግበሪያ ማበልፀጉን ገለጸ፡፡

ቦርዱ የተለያዩ የምርጫ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ማቀዱን ያስታወቀ ሲሆን የዕጩዎችንና የመራጮችን ምዝገባ በቴክኖሎጂ አስደግፎ ማከናወን የሚያስችሉ መተግበሪያዎች ማበልጸጉን ጠቅሷል፡፡

በቴክኖሎጂ ዝግጅቱ ዙሪያ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ውይይት በማድረግ ግብዓት ለማሰባሰብ ያለመ መድረክ በአዲስ አበባ እያካሄደ ይገኛል።


 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሃይሉ በዚሁ ወቅት፤ ቦርዱ በቴክኖሎጂ የታገዘ የምርጫ አስተዳደር ሥርዓትን ለመተግበር እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም በሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ የዕጩዎችንና የመራጮችን ምዝገባ በቴክኖሎጂ ለማከናወን አስፈላጊ የሚባሉ መተግበሪያዎች መበልጸጋቸውን ተናግረዋል።

በዚህም በመጪው ምርጫ የዕጩዎች ምዝገባ ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ የሚከናወን እንደሚሆን በመጥቀስ መተግበሪያዎቹ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የበለጸጉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።


 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቴክኒካል ቡድን ማናጀር አቶ ሰናይ አምደወርቅ መተግበሪያዎቹ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህም በርካታ ቁጥር ያላቸውን መራጮች እንዲሁም ዕጩዎች ካሉበት ቦታ ሆነው እንዲመዘገቡ የሚያስችሉ መሆናቸውን ጠቁመው አሰራሩ ወጪን፣ ጊዜንና ጉልበትን እንደሚቀንስም ገልጸዋል።

በውይይቱ የተገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ሂደቱ የኢትዮጵያን ምርጫ ወደፊት ማራመድ የሚያስችልና ግልፅነትና ተጠያቂነት ለማስፈን ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ስራ አስፈጻሚና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል መብራቱ አለሙ(ዶ/ር) መተግበሪያው ጊዜ ቆጣቢና እንግልት የሚቀንስ መሆኑን ገልጸው፤ ለግልፅነትና ተጠያቂነት ምቹ መደላድል የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል፡፡


 

የመላው ሲዳማ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ፓርቲ ሊቀ-መንበር ተስፋማርያም ጉቻ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ወደ ቴክኖሎጂ እያደረገች ያለችው ሽግግር የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መተግበሪያዎቹ አንድ ፓርቲ ካለበት ቦታ በመሆን እጮዎቹን በቀላሉ ማስመዝገብ የሚያስችል በመሆኑ ጊዜና ወጪን ቆጣቢ ነው ብለዋል፡፡  


 

የወሎ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ነጻነት ጣሰው የምርጫ ቦርድ የምርጫ ሂደቶችን ለማዘመን እያደረገ ያለው ተግባር የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም