የዴሞክራሲ ተቋማትን በማጠናከር መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የተከናወኑ ተግባራት መጠናከር አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የዴሞክራሲ ተቋማትን በማጠናከር መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የተከናወኑ ተግባራት መጠናከር አለባቸው

አዳማ ፣ሰኔ 2/2017 (ኢዜአ)፡- መንግስት የዴሞክራሲ ተቋማትን በማጠናከር መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ያከናወናቸው ተግባራት መጠናከር እንደሚገባቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ አሳሰቡ።
የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የመልካም አስተዳደርና አስተዳደራዊ ፍትህ ክዋኔንና የተቋሙን የአምስት ዓመት መሪ እቅድ ግምገማ መድረክ አካሄዷል።
በግምገማ መድረኩ ላይ የተገኙት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ እውነቴ እንዳሉት የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ሂደት አጭር ቢሆንም በዜጎች ላይ የሚደርሱ አስተዳደራዊ በደሎችን በመፍታት ረገድ ለውጥ ማምጣታቸውን አስረድተዋል።
ይህንን ይበልጥ በማሳደግ የተቋማቱን የህዝብ አመኔታ ለማጉላትና አሰራራቸውን እንዲያዘምኑ ምክር ቤቱ ድጋፍ ማድረጉን አንስተዋል።
መንግስት የዴሞክራሲ ተቋማትን በማጠናከር መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን በማድረግ ረገድ ያላቸውን አበርክቶ ለማጉላት ይበልጥ መስራት ይገባል ብለዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ዝናሽ ጸጋዬ ተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጥ ቅሬታዎችን የፈታበትን መንገድ በሪፖርትና በመስክ ክትትል ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።
ይህም ለመልካም አስተዳደር መስፈን የበኩሉን ድርሻ ማበርከቱን አንስተዋል።
የህዝብ አገልግሎቶች አሳታፊ ሆነው ተቋማዊ ተጠያቂነትን ለማምጣት እንዲችሉ የዴሞክራሲ ተቋማት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ያነሱት ደግሞ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የሙያዊ ዘርፍ ኃላፊና ምክትል ዋና ጸሀፊ ንጉሴ መሸሻ ናቸው።
እየሰፋ የመጣውን የህዝብ አገልግሎት በጥራትና በፍጥነት ተደራሽ በማድረግ ሂደት የሚገጥሙ የተገልጋይ ቅሬታዎችን በመፍታት ለመልካም አስተዳደር መስፈን ተቋሙ የበኩሉን ድርሻ ማበርከቱን አክለዋል ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ ስመኝ ውቤ እንዳሉት አስፈፃሚ አካላት እና የግል ድርጅቶች የሚሰጧቸው አገልግሎቶች ለአስተዳደራዊ በደል እንዳይጋለጡና ሲፈጸሙም እልባት እንዲያገኙ መሰራቱን ተናግረዋል።
የተቋሙን አሰራር በማዘመንም አስተዳደራዊ በደሎች በፍጥነት የሚፈቱበትን ቀልጣፋ ስርዓት ለመዘርጋት ተቋማዊ መዋቅርና ዲጂታላይዜሽን ላይ ትኩረት መሰጠቱን አስረድተዋል።