ኢትዮጵያ መድን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ማንሳቱን አረጋገጠ 

አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 2/2017 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ መድን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ለመጀመሪያ ጊዜ ማንሳቱን አረጋግጧል።

ዛሬ ረፋድ ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደ የ34ኛ ሳምንት ጨዋታ መቀሌ 70 እንደርታ እና ኢትዮጵያ ቡና አንድ አቻ ተለያይተዋል።

ዩጋንዳዊው ጂኦፍሪ ዋሳዋ በ54ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ ኢትዮጵያ ቡናን መሪ አድርጓል።

ይሁንና መሉጌታ ወልደጊዮርጊስ በ64ኛው ደቂቃ ከመረብ ላይ ያሳረፋት ግብ መቀሌ 70 እንደርታን አቻ አድርጋለች።


 

ኢትዮጵያ ቡና ነጥብ መጣሉን ተከትሎ ኢትዮጵያ መድን ሶስት ጨዋታዎች እየቀሩት  የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ለመጀመሪያ ጊዜ ማንሳቱን አረጋግጧል።

በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው ኢትዮጵያ መድን በቀጣዩ ዓመት ኢትዮጵያን ወክሎ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ ይሳተፋል።

ኢትዮጵያ ቡና በ56 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።

መቀሌ 70 እንደርታ በ38 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

የ34ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ከሰዓትም ቀጥሎ ሲውል ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከሃዋሳ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሀድያ ሆሳዕና ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም