ሰባተኛውን ሀገራዊ ምርጫ በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ - ኢዜአ አማርኛ
ሰባተኛውን ሀገራዊ ምርጫ በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ
አዲስ አበባ፤ሰኔ 2/2017 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰባተኛውን ሀገራዊ ምርጫ በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ ገለጸ።
ቦርዱ የተለያዩ የምርጫ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ማቀዱን ያስታወቀ ሲሆን ከነዚህም መካከል የዕጩዎችንና የመራጮችን ምዝገባ በቴክኖሎጂ አስደግፎ ለማከናወን የተያዘው ዕቅድ ይጠቀሳል።
ቦርዱ በቴክኖሎጂ ዝግጅቱ ዙሪያ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ውይይት በማድረግ ግብዓት ለማሰባሰብ ያለመ መድረክ በአዲስ አበባ እያካሄደ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሃይሉ በዚሁ ወቅት፤ቦርዱ በቴክኖሎጂ የታገዘ የምርጫ አስተዳደር ሥርዓትን ለመተግበር እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም በሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ የዕጩዎችንና የመራጮችን ምዝገባ በቴክኖሎጂ ለማከናወን አስፈላጊ የሚባሉ መተግበሪያዎች መበልጸጋቸውን ተናግረዋል።
በዚህም በመጪው ምርጫ የዕጩዎች ምዝገባ ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ የሚከናወን እንደሚሆን በመጥቀስ አሰራሩ ወጪን፣ ጊዜንና ጉልበትን የሚቀንስ መሆኑን ገልጸዋል።
መተግበሪያዎቹ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የበለጸጉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።