መውረድ የሚያሰጋቸው ክለቦች የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ 

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 2/2017 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ34ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ ሶስት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ መቀሌ 70 እንደርታ እና ኢትዮጵያ ቡናን ከጠዋቱ 3 ሰዓት ከ30 ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ያገናኛል።

መቀሌ 70 እንደርታ በ37 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። 

ቡድኑ ማሸነፍ ላለመውረድ እያደረገ ላለው ትግል ወሳኝ ሶስት ነጥብ እንዲያገኝ ያስችለዋል። 

ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና በ55 ነጥብ 2ኛ ደረጃን ይዟል። ቡናማዎቹ ማሸነፍ በሊጉ ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል እንዲመለስ ያደርገዋል።

ቡድኑ ከተሸነፈ ወይም አቻ ከወጣ የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ዋንጫውን ማንሳቱን ያረጋግጣል። 

ቀን 9 ሰዓት ላይ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከሃዋሳ ከተማ ይጫወታሉ።

ከሊጉ የወረደው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ19 ነጥብ የመጨረሻውን 18ኛ ደረጃን ይዟል።

ሃዋሳ ከተማ በ44 ነጥብ 7ኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ ባለፉት 10 የሊግ ጨዋታዎች አልተሸነፈም።

በዕለቱ የመጨረሻ መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ሀድያ ሆሳዕና ምሽት 12 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

የአምናው የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ40 ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል። ማሸነፍ ቡድኑ ከስምንት የሊጉ ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት እንዲመለስ እና ከወራጅ ቀጠና ክልል እንዲርቅ ያስችለዋል።

በ44 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ሀድያ ሆሳዕና ባለፉት አራት የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፈም። ማሸነፍ ወደ ድል መንገድ ይመልሰዋል።

ሶስት ነጥብ የሀድያ ሆሳዕናን ደረጃን በጊዜያዊነት ወደ 4ኛ ከፍ ያደርጋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም