ፖርቹጋል ስፔንን በማሸነፍ የዩኤፋ ኔሽንስ ሊግ ዋንጫ አነሳች - ኢዜአ አማርኛ
ፖርቹጋል ስፔንን በማሸነፍ የዩኤፋ ኔሽንስ ሊግ ዋንጫ አነሳች

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 1/2017 (ኢዜአ)፦ በዩኤፋ ኔሽንስ ሊግ ኤ ሻምፒዮንሺፕ የፍጻሜ ጨዋታ ፖርቹጋል ስፔንን በመለያ ምት በማሸነፍ ዋንጫውን አንስታለች።
ማምሻውን በአሊያንዝ አሬና ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ኑኖ ሜንዴዝ እና ክርስቲያኖ ሮናልዶ ለፖርቹጋል ጎሎቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ማርቲን ዙቢሜንዲ እና ማይክል ኦያርዛባል ለስፔን ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ጨዋታው በመደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሁለት አቻ በመጠናቀቁ ተጨማሪ 30 ደቂቃ ተጨምሯል።
በጭማሪ ሰዓትም ግብ ባለመቆጠሩ ጨዋታው ወደ መለያ ምት አምርቷል።
በዚህም ፖርቹጋል ስፔንን 5 ለ 3 በማሸነፍ የኔሽንስ ሊግን ዋንጫን ለሁለተኛ ጊዜ አንስታለች።
ከስፔን በኩል አልቫሮ ሞራታ ፍጹም ቅጣት ምት ስቷል።
ውድድሩን ለሁለት ጊዜ በማሸነፍ የመጀመሪያዋ ሀገር ሆናለች። ቡድኑ እ.አ.አ 2019 ውድድሩ ሲጀመር የመጀመሪያው አሸናፊ ነበረች።
ለውድድሩ ፍጻሜ ለሶስት ተከታታይ ጊዜ ለፍጻሜ የደረሰችው ስፔን ዋንጫውን ሳታገኝ ቀርታለች። የዋንጫ ክብሯንም ማስጠበቅ አልቻለችም።
ቀን ላይ በተደረገ ጨዋታ ፈረንሳይ ጀርመንን በኪሊያን ምባፔ እና ማይክል ኦሊሴ ግቦች 2 ለ 0 በማሸነፍ በውድድሩ ሶስተኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች።