አዳማ ከተማ ወሳኝ ድል ተቀዳጅቷል - ኢዜአ አማርኛ
አዳማ ከተማ ወሳኝ ድል ተቀዳጅቷል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 1/2017 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ34ኛ ሳምንት ጨዋታ አዳማ ከተማ ስሑል ሽሬን 4 ለ 2 አሸንፏል።
ማምሻውን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ቢንያም አይተን ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር አድናን ረሻድ እና የስሑል ሽሬው ሰለሞን ገብረክርስቶስ በራሱ ግብ ላይ ቀሪዎቹን ግቦች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ብርሃኑ አዳሙ እና አላዛር ሽመልስ ለስሑል ሽሬ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
አዳማ ከተማ በሊጉ አራተኛ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል። በ38 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ቢገኝም አሁንም ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ቡድኑ 13ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና 14ኛ ደረጃን ከያው ፋሲል ከነማ ጋር በነጥብ እኩል ሆኗል።
በአንጻሩ ከሊጉ የወረደው ስሑል ሽሬ በ22 ነጥብ 17ተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቡድኑ 16ኛ ሽንፈቱን አስተናግዷል።
በሊጉ ላለመውረድ እየተደረገ ያለው ፋክክር የበለጠ አጓጊ ሆኗል።
ቀን ላይ በተደረገ የ34ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።