የቱሪስት መስህቦችን፣ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ቅርሶችን ሰንዶ ለልጆች ማስተማር ይገባል - ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ - ኢዜአ አማርኛ
የቱሪስት መስህቦችን፣ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ቅርሶችን ሰንዶ ለልጆች ማስተማር ይገባል - ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 1/2017(ኢዜአ)፦ የቱሪስት መስህቦችን፣ ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ቅርሶችን ሰንዶ ለልጆች ማስተማር እንደሚገባ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ገለጹ።
በኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነጋ ወዳጆ የተጻፉ ሁለት የሕፃናት መጽሐፍት ዛሬ ተመርቀዋል።
በምረቃ መርኃግብሩ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፣ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ዱጋ፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አብዱላዚዝ ዳውድ(ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
መጽሐፍቱ የቱሪዝም መስህቦችን፣ ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ ቅርሶችን የሚዳስሱ ሲሆን የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሀ፣ ሁ(ABC’s of Ethiopian Tourism) እና ABC Tuuriizimii oromiyaa በሚሉ ርዕሶች የተዘጋጁ ናቸው።
የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በመርሃ ግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት ኢትዮጵያ ያላትን በርካታ የቱሪዝም ሃብቶች ይዘታቸውን ሰንዶ ለትውልድ በማስተላለፍ ልጆች ላይ መስራት ይገባል።
በዛሬው ዕለት ለምረቃ የበቁት መጽሐፍት ልጆች የሀገራቸውን ታሪክና ባህል እንዲሁም የቱሪዝም ሀብቶች እንዲያውቁ የሚያግዙ ናቸው ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አብዱላዚዝ ዳውድ(ዶ/ር) በበኩላቸው መጽሐፍቱ የቱሪዝም ሀብቶችን ለትውልድ ማስተማር የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ይህም የቱሪዝም ሀብቶች ይዘታቸው ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ ያስችላል ነው ያሉት።
መጽሐፍቱን ያዘጋጁት የኦሮሚያ ክልል ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነጋ ወዳጆ እንደገለጹት መጽሐፍቱ ልጆች የሀገራቸውን የቱሪስት መስህቦች፣ ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ ቅርሶችን ሊረዱት በሚችሉት ልክ የተዘጋጁ ናቸው።