በዜጎች ላይ ለሚደርሱ አስተዳደራዊ በደሎች መፍትሔ እና ምላሽ በማሰጠት በኩል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዜጎች ላይ ለሚደርሱ አስተዳደራዊ በደሎች መፍትሔ እና ምላሽ በማሰጠት በኩል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው
አዳማ፤ ሰኔ 1/2017(ኢዜአ)፡- በዜጎች ላይ ለሚደርሱ አስተዳደራዊ በደሎችን መርምሮ ምላሽ እና መፍትሔ በማሰጠት በኩል በተጠናከረ መልኩ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ።
ተቋሙ በመልካም አስተዳደር፣ በአስተዳደራዊ ፍትህ ክዋኔና የተቋሙን የአምስት አመት መሪ ዕቅድ በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ እየመከረ ነው።
በመድረኩ የተቋሙ ዋና ዕንባ ጠባቂ ስመኝ ውቤ፤ በህግ የተደነገጉ የሰዎች መብቶችና ጥቅሞች መከበራቸውን በማረጋገጥ የህግ የበላይነትን ለማስፈን እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
በተለይም የአስፈጻሚ አካላት ጥራት፣ ቅልጥፍና እና ግልፅነት ያለው የመንግስት አስተዳደርና የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲሰፍን በልዩ ትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የመንግስት አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች የሚሰጧቸው አገልግሎቶች ከመልካም አስተዳደር መርሆዎችና ከዜጎች መብት አንጻር ህግና አሰራርን መከተላቸውን ቁጥጥር በማድረግ ክፍተቶች እንዲታረሙ እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።
በመሆኑም በዜጎች ላይ የሚደርሱ አስተዳደራዊ በደሎችን መርምሮ ምላሽና መፍትሔ በማሰጠት በኩል በተጠናከረ መልኩ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የተቋሙ ምክትል ዋና ዕንባ ጠባቂ የኔነህ ስመኝ(ዶ/ር)፤ በትምህርት፣ በፕሮጀክቶች አፈጻጸም፣ በመሬት ሀብት አጠቃቀምና በኢንቨስትመንት ላይ የቀረቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የተፈቱበትን አግባብ አስረድተዋል።
በቀጣይ መንግስት ለህዝብ ያለውን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ አስተዳደራዊ በደል እንዲቀረፍና ሲፈጸምም እንዲፈታ ማድረግ ላይ በሚጠበቀው ልክ እንደሚሰራም አመላክተዋል።
ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ ዜጎች ለሚደርስባቸው በደል ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመድረኩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ፣ ሌሎች የስራ ኃላፊዎችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።