የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ34ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ34ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 1/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 34ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ ይጀመራል።
የ34ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ በአርባ ምንጭ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ መካከል ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይደረጋል።
አርባምንጭ ከተማ በ42 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ ካሸነፈ በሊጉ ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን ያስመዘግባል።
የ16 ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ44 ነጥብ 9ኛ ደረጃን ይዟል።
መርሃ ግብሩ በ33ኛ ሳምንት ከሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ጋር አቻ ከወጣበት ጨዋታ በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርገው ነው።
ምሽት 12 ሰዓት ላይ ስሑል ሽሬ ከአዳማ ከተማ ይጫወታሉ።
ወደ ከፍተኛ ሊግ የወረዳው ስሑል ሽሬ በ22 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ ባለፉት 15 የሊግ ጨዋታዎች ድል አልቀናውም።
ቡድኑ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በመቀጠል (16 ጊዜ) በሊጉ በርካታ ሽንፈቶች (15 ጊዜ) አስተናግዷል። በሊጉ ያሸነፈው ሶስት ጊዜ ብቻ ነው።
ባለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች ድል የቀናው አዳማ ከተማ በበኩሉ በ35 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
አዳማ ከተማ በዛሬው ጨዋታ ማሸነፍ ላለመውረድ እያደረገ ባለው ፉክክር ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያስገኝለታል።
የ34ኛ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ ሰኔ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።