ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የሚወክለው ክለብ ማን ይሆን?  

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 1/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ በወላይታ ድቻ እና ሲዳማ ቡና መካከል ዛሬ ይደረጋል።

ጨዋታው ከቀኑ 9 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳል። 

ወላይታ ድቻ በግማሽ ፍጻሜው ሸገር ከተማን በዘላለም አባተ እና ብዙአየሁ ሰይፈ ግቦች በማሸነፍ ለፍጻሜ ማለፉ ይታወቃል።

ቡድኑ ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት ለኢትዮጵያ ዋንጫ ፍጻሜ በማለፍ በውድድሩ ላይ ያለውን ጠንካራ ብቃት አሳይቷል።

ወላይታ ድቻ በ2016 ዓ.ም ለፍጻሜ ደርሶ በኢትዮጵያ ቡና 2 ለ 1 መሸነፉ የሚታወስ ነው።

በ2009 ዓ.ም መቻል በመርታት የውድድሩ አሸናፊ በመሆን ኢትዮጵያን ወክሎ በካፍ ኮንፌዴሬሽ ዋንጫ መሳተፉ ይታወቃል። 

በአንጻሩ ተጋጣሚው ሲዳማ ቡና በግማሽ ፍጻሜው መቻልን በመለያ ምት 7 ለ 6 በማሸነፍ ለፍጻሜ አልፏል።

ሲዳማ ቡና ለኢትዮጵያ ዋንጫ ፍጻሜ ሲያልፍ በ21 ዓመት የክለቡ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። 

ወላይታ ድቻ የኢትዮጵያ ዋንጫን ለሁለተኛ ጊዜ፣ ሲዳማ ቡና ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማንሳት ይፋለማሉ።

ሁለቱ ክለቦች በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለት ጊዜ ተገናኝተዋል።

ግንቦት 8 ቀን 2017 ዓ.ም ባደረጉት የ30ኛ ሳምንት ጨዋታ ሲዳማ ቡና በጋናዊው አጥቂ ማይክል ኪፕሩቪል ጎል ወላይታ ድቻን 1 ለ 0 አሸንፏል። 

ቡድኖቹ ጥር 11 ቀን 2017 ዓ.ም በ15ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ተገናኝተው ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል።

የጨዋታው አሸናፊ በቀጣይ ዓመት ኢትዮጵያን ወክሎ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ይሳተፋል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት በዝግ ስታዲየም እንደሚደረግ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

በፍጻሜው ጨዋታ ምክንያት በ34ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር ወላይታ ድቻ ከባህር ዳር ከተማ እና ሲዳማ ቡና ከድሬዳዋ ከተማ ሊያደርጓቸው የነበሩ ጨዋታዎች ወደ ሰኔ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ተሸጋግረዋል። 

በ1937 ዓ.ም የተጀመረው የኢትዮጵያ ዋንጫ የ80 ዓመት ታሪክ ያለው አንጋፋ ውድድር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም