ቀጥታ፡

ለምግብ ደህንነት መጠበቅ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራርን ማጎልበት ይገባል

አዲስ አበባ፤ግንቦት 30/2017 (ኢዜአ)፦ለምግብ ደህንነት መጠበቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ የኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሔራን ገርባ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን በጋራ የአለም የምግብ ደህንነት ቀንን "ሳይንስን በተግበር" በሚል መሪ ሃሳብ በፓናል ውይይት አስበው ውለዋል።

የኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሔራን ገርባ በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ የዘንድሮው የአለም የምግብ ደህንነት ቀን ሲከበር ከእርሻ እስከ ጉርሻ ባለው የምግብ እሴት ሰንሰለት ውስጥ ለሚሳተፉ አካላት ስለ ምግብ ደህንነት አጠባበቅ ሳይንሳዊ ግንዛቤዎችን ለማስያዝ ነው፡፡

ለምግብ ጥራት መጠበቅ አምራቾች፣ አቀናባሪዎች፣አከፋፋዮች፣ ቸርቻሪዎችና ተጠቃሚዎች ትልቅ ድርሻ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

እነዚህ አካላት በምግብ እሴት ሰንሰለት ውስጥ ምግቦች ሳይበለሹ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የማከማቸትም ሆነ የማጓጓዝ ስራቸውን በህንነቱ በተጠበቀ መልኩ መሆን እንዳለበት አመላክተዋል፡፡

በዚህ ሒደት ውስጥ ለምግብ ደህንነት መጠበቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣንም ህጎችንና መመሪያወችን በማውጣት ለምግብ ደህንነት መጠበቅ ከመቸውም ጊዜ በላይ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲቱዩት ዋና ዳይሬክተር መሰረት በቀለ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ጤናን የሚጎዱ ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶች እንዳይመረቱ እና እንዳይሰራጩ ከተቆጣጣሪ ተቋማት ጋር በቅንጀት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም አበረታች ውጤቶች መመዝበባቸውን ገልጸው፤ በቀጣይም ኢንስቲትዩቱ ምርቶች በተቀመጠላቸው ስታንዳርድ መሰረት እንዲመረቱ ደረጃዎችን የማውጣት ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን የእንስሳት ምርት ሬጉላቶሪ መሪ ስራ አስፈታሚ አያሌው ሹመት (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ባለስልጣኑ ምርቶች ወደ ምግብ ከመቀየራቸው በፊት የጥራት ቁጥጥር ስራ እንደሚሰራ አመላክተዋል።

የወተት ላሞች ጥራት ያለው ወተት እንዲሰጡ ጥራት ያለው መኖ ማቅረብ ይገባል፤ጥራት ያለው የሰብል ምርት ለማምረት ምርጥ ዘር መጠቀም ግዴታ ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ባለስልጣኑ በሰብልም ሆነ በእንስሳት ዘርፍ ጥራት ያላቸውን ምርቶች እንዲመረቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል፡፡

በአለም ላይ በምግብ ደህንነት አለመጠበቅ ምክንያት በየአመቱ በርካታ ሰዎች ለምግብ ወለድ በሽታዎች እንደሚጋለጡ የተናገሩት ደግሞ በአለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ የአቅርቦት ሰንሰለት ሃላፊ ሲልቪያ ክላራ ናቸው፡፡

በመሆኑም በኢትዮጵያ የምግብ ደህንነትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ እየተሰሩ ባሉ ስራዎች የአለም ምግብ ፕሮግራም ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የዘንድሮው የአለም የምግብ ደህንነት ቀን ሲከበር በአለም ለ7ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ6ኛ ጊዜ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም