በኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለጤና፣ለግብርናና ለኃይል አቅርቦት ዘርፎች መጠቀም የሚያስችል ጥናትና ምርምር እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፤ግንቦት 30/2017(ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ኒውክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከል ሆኖ መመረጡ ይታወቃል።

በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ማዕከል ኃላፊ ደረጃው አየለ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፥ዩኒቨርሲቲው ከኒውክሌር ኢነርጂ ሰላማዊ የኃይል አማራጭ ተጠቃሚ የሚያደርጋትን የልህቀት ማዕከላት ገንብቷል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የአፍሪካ የኒውክሌር ሳይንስ ማዕከል ሆኖ መመረጡ በዘርፉ ስኬታማ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ለመሥራት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

በማዕከሉ በተለያዩ የምርምር መስኮች ላይ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር ትልልቅ የጥናትና ምርምር ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በቀጣይም በኒውክሌር ቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎትን ካካበቱ የሩሲያ፣ ኮሪያና ቻይና ተመራማሪና የልህቀት ማዕከላት ጋር ጠንካራ ትብብር በመፍጠር እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለጤና፣ለግብርናና ለኃይል አቅርቦት ዘርፎች መጠቀም የሚያስችል ጥናትና ምርምር እየተካሄደ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርስቲው የ2ተኛ ዓመት የኒውክሌር ሳይንስ ኢንጂነርንግ ተማሪ ቴዎድሮስ አበባው፥ በዩኒቨርሲቲው የኒውክሌር ትምህርት መሰጠቱ ኢትዮጵያን በዘርፉ ተጠቃሚ የሚያደርግ ዕውቀትና ክህሎት ያለው ዜጋ ለማፍራት ትልቅ ዕድል መፍጠሩን ገልጿል።

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ የኒውክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከል ሆኖ የተመረጠ ሲሆን በማስተርስ ዲግሪ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል።

በሚያዝያ ወር መጨረሻ የዓለም አቀፍ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲና የቻይናው ሽንግዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር፣በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ሥር የአፍሪካ ኒውክሌር ሳይንስ ማዕከል እንዲቋቋም ስምምነት ማድረጋቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም