ምክር ቤቶች በሀገረ መንግስት ግንባታ ውስጥ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቶች በሀገረ መንግስት ግንባታ ውስጥ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው
አዳማ፤ግንቦት 30/2017(ኢዜአ)፡-ምክር ቤቶች በሀገረ መንግስት ግንባታ ውስጥ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው ሲሉ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የመንግስታት ግንኙነት፤የዴሞክራሲ አንድነትና የህገ መንግስት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ ፀሓፊ ወይዘሮ ባንችይርጋ መለሰ እንደገለጹት፤።
''የመንግስታት ግንኝነት ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታና የምክር ቤቶች ሚና'' በሚል መሪ ሀሳብ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አመራሮች የተዘጋጀ የምክክር መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው።
በተለይም የመንግሥታት ግንኙነትን ማጠናከር ክፍቶችን በመሙላት ሕብረ ብሔራዊ የፌዴራል ስርዓትን ጠንካራ መሰረት ላይ ለማቆም ያግዛል ብለዋል።
ምክር ቤቶችም የመንግስታት ግንኙነትን ለመደንገግ የወጡ የአሰራርና የህግ ማዕቀፎችን ተፈፃሚነት በመከታተል ረገድ ትልቅ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።
የሀገረ መንግስት ግንባታ እውን እንዲሆንና የተሳለጠ ሕብረብሔራዊ የፌዴራል ስርዓትን ለማፅናት በትኩረት መሰራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የመንግሥታት ግንኙነትን ለማጠናከር፣ዘላቂ ሰላም ለማፅናትና ልማትን ለማፋጠን እንዲሁም አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠርም መስራትም እንዲሁ።
በሚኒስትር ማዕረግ የኢትዮጵያ የህግና ፍትህ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ በበኩላቸው፥ጠንካራ የሀገረ መንግሥት ግንባታ እውን ለማድረግ የተናበበ እና በመርህ ላይ የተመሰረተ የመንግስታት ግንኙነት ያስፈልጋል ብለዋል።
በተለይም በመንግስታት መካከል መተማመን እንዲጠናከር፣ሰላምን ለማፅናትና ልማትን ለማስቀጠል ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።
በመድረኩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሜቴዎች ሰብሳቢዎችና አመራሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።