በጉጂ ዞን የድርቅ ተጋላጭነትን ለመቋቋም በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ ስራዎች ለውጥ እየታየ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጉጂ ዞን የድርቅ ተጋላጭነትን ለመቋቋም በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ ስራዎች ለውጥ እየታየ ነው

ነገሌ ቦረና፣ግንቦት 30/2017(ኢዜአ)፦በጉጂ ዞን ባለፉት አመታት የድርቅ ተጋላጭነትን ለመቋቋም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተሰራ ስራ ለውጥ እየታየ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡
በጽህፈት ቤቱ የተፈጥሮ ሀብት ቡድን መሪ አቶ ወንዶ ሸርቦቴ፤ በዞኑ ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች በ22 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ መተከላቸውን ገልጸዋል።
የተተከሉ ችግኞችም በህዝብ ተሳትፎ እንክብካቤና ጥበቃ ተደርጎ በስፋት መጽደቅ ማስቻሉን ተናግረዋል።
ከተተከሉት ችግኞች የደን፣ የጥላ ዛፍ፣ የእንስሳት መኖና የፍራፍሬ ችግኞች ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑም ለአብነት አንስተዋል፡፡
ድርቅና የአካባቢ መራቆትን በዘላቂ ልማት ለመቋቋም በተመሳሳይ በዘንድሮም ከ87 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል፡፡
ለዚህም በ13ቱም ወረዳዎች በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ምክንያት የተራቆተ ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ የችግኝ መትከያ መሬት መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
በጽህፈት ቤቱ የደን አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ቴድሮስ ገብሬ፤ ለአረንጓዴ አሻራ የተሰጠው ትኩረት የአካባቢ መራቆትን እየታደገ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በዞኑ በተሰራው ስራ ምንጮች እየጎለበቱ ከአመት አመት እየፈሰሱ እንደሆነና መጠለያ አጥተው የተሰደዱ የዱር እንስሳት ጭምር እየተመለሱ መሆኑን ተናግረዋል።
በዞኑ ከ6 አመታት በፊት ከ274 ሺህ ሄክታር በታች የነበረው የዞኑ ደን ሽፋንም ወደ 382 ሺህ ሄክታር ከፍ ማለቱን ጠቅሰዋል፡፡
ችግኝ ከመትከል ጎን ለጎን የዞኑ ህዝብ ተሳትፎ ድጋፍና ትብብር ለደን ልማት ሽፋኑ መጨመር ከፍተኛ ድርሻ ማበርከቱንም ነው የተናገሩት፡፡