ሕብረተሰቡ የባቡር መሰረተ ልማቶችን በአግባቡ በመጠቀምና በመጠበቅ ሀገራዊ ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ሕብረተሰቡ የባቡር መሰረተ ልማቶችን በአግባቡ በመጠቀምና በመጠበቅ ሀገራዊ ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል
አዲስ አበባ፤ግንቦት 30/2017 (ኢዜአ)፦ሕብረተሰቡ የባቡር መሰረተ ልማቶችን በአግባቡ በመጠቀምና ተገቢውን ጥበቃ በማድረግ ሀገራዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ጥሪ አቀረበ።
የትራንስፖርት መሰረተ ልማቶች መሟላት ፈጣን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን በማሳለጥ ለአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ መረጋጋት ጉልህ ሚና ይጫወታሉ።
በኢትዮጵያ የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማሳደግና የገቢና ወጪ ንግዱን ለማሳለጥ የባቡር መሰረተ ልማቶች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።
ይሁንና በእነዚህ መሰረተ ልማቶች ላይ ከአጠቃቀም ጉድለትና የባለቤትነት ስሜት ማጣት ምክንያት ተደጋጋሚ ጉዳቶች ሲደርሱ ይስተዋላል።
ይህም የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱን በማስተጓጎል ተጠቃሚውን ለአላስፈላጊ ወጪና እንግልት እንዲሁም በሀገር ሃብት ላይ ኪሳራ ያደርሳል።
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ኢንጅነር ህሊና በላቸው ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኮርፖሬሽኑ የሚገነባቸው የባቡር መሰረተ ልማቶች ከፍተኛ የአገር ሃብት የፈሰሰባቸው ናቸው።
ኮርፖሬሽኑ ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ የተለያዩ የሪፎርም ስራዎችን በማከናወን በራስ አቅም የመሰረተ ልማቶችን ለመገንባት ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ የማማከርና የመልቲሞዳል ፍቃድ አግኝቶ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።
ይህም የሎጂስቲክስ አገልግሎቱን የበለጠ ለማሳደግና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን ለማሳለጥ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
በከፍተኛ ወጪ የሚገነቡት የባቡር መሰረተ ልማቶች በአግባቡ ካልተጠበቁ የታለመላቸውን የረጅም ጊዜ አገልግሎት እንደማይሰጡ አመልክተዋል።
በመሰረተ ልማቶቹ ላይ ተደጋጋሚ ጉዳት እንደሚደርስ ጠቁመው፣ሕብረተሰቡ መሰረተ ልማቶቹን በአግባቡ በመጠቀም አገራዊ ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
የባቡር መሰረተ ልማቶቹ ባሉባቸው አካባቢዎች ከሕብረተሰቡ ጋር በመወያየት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እንደሚሰሩን አመልክተዋል።
ከጸጥታ አካላትና ከየአካበቢው ኮሚኒቲ ፖሊስ ጋር በመሆን የመሰረተ ልማቱ ተገቢውን ጥበቃ እንዲያገኝ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።