በአዲስ አበባ ለውጡን የሚመጥን የደንብ ማስከበር ተቋም እየተገነባ ነው

አዲስ አበባ፤ግንቦት 30/2017 (ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ ለውጡን የሚመጥን የደንብ ማስከበር ተቋም እየተገነባ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ሀላፊ ሊዲያ ግርማ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ለ6ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን ፓራ ሚሊተሪ ኦፊሰሮች ዛሬ እያስመረቀ ነው።

ኦፊሰሮቹ 2 ሺህ 74 ሲሆኑ በፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የንድፈ ሀሳብና ወታደራዊ ስልጠናዎችን የተከታተሉ ናቸው።

በምርቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ ጃንጥራር አባይ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ ሊዲያ ግርማ፣ የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራን ጨምሮ ፖሊስ ኮሚሽነሮችና የመዲናዋ አመራር አባላት ተገኝተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ ሊዲያ ግርማ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በመዲናዋ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በርካታ የለውጥ ስራዎች እየተከናወኑ ነው።

እየተመዘገበ ያለውን ለውጥ ዘላቂ ለማድረግም የጸጥታ ተቋማትን የማጠናከር ተግባራት በተሳለጠ አግባብ እየተካሄደ ነው ብለዋል።

ለውጡን የሚመጥን የደንብ ማስከበር ተቋም እየተገነባ መሆኑን ገልጸው፤ የዛሬ ተመራቂዎችም የዚሁ አካል ነው ብለዋል።

መሬት ወረራን በመከላከል፣የወንዞች አካባቢ ጽዳት እንዲሁም መሰረተ ልማት ደህንነት እንዲጠበቅ የደንብ ማስከበር ሚና ትልቅ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል መስፍን አበበ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ለደንብ ማስከበር ኦፊሰሮች የተግባር እና ንድፈ ሀሳብ ስልጠና መሰጠቱን ጠቅሰዋል።

ተመራቂዎች በስልጠና ቆይታቸው የቀሰሙትን እውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ ግዳጃቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ተመራቂዎች ህገ ወጥነትን ለመከላከል የለውጥ ሀዋሪያ መሆን አለባቸው ብለዋል።

የዛሬ ተመራቂዎች የተቋሙን ደንብ የማስከበር አቅም እንደሚያሳድገውም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም