የመዲናዋን ለውጥ በሕግ እና በስርዓት ለመምራት የሚያስችሉ ማሻሻያዎች እየተደረጉ ነው -ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የመዲናዋን ለውጥ በሕግ እና በስርዓት ለመምራት የሚያስችሉ ማሻሻያዎች እየተደረጉ ነው -ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 30/2017 (ኢዜአ)፦የመዲናዋን ለውጥ በሕግ እና በስርዓት ለመምራት የሚያስችሉ ማሻሻያዎች እየተደረጉ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለስልጣን የስድስተኛ ዙር ፖራሚሊተሪ ሰልጣኝ ኦፊሰሮችን ኮልፌ በሚገኘው አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሌጅ አስመርቋል።
በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ምክትል ከንቲባ ዣንጥራር አባይ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ፣ ፣የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል እና የኢትዮጵያ ፖሊሲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት መስፍን አበበ እና ሌሎች የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
2 ሺህ 74 ምልምል የፖራ -ሚሊተሪ ኦፊሰሮቹ በአዲስ አበባ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት ወራት የንድፈ ሀሳብ እና ወታደራዊ ስልጠና ወስደዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በንድፈ ሀሳብ እና ተግባር ስልጠናውን ወስደው ለምረቃ የበቁ ፓራሚሊተሪ ኦፊሰሮችን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
አዲስ አበባ ከተማ ሁለንተናዊ እና ፈጣን ለውጥ እየመጣ እንደምትገኝ ገልጸዋል።
የመዲናዋን ለውጥ በሕግ እና በስርዓት ለመምራት የሚያስችሉ ማሻሻያዎች እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በዚህ ረገድም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሕግን የሚያስከብር የደንብ ኦፊሰርን በማሰልጠን እንዲሰማሩ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ዛሬ የተመረቁ ፖራሚሊተሪ ኦፊሰሮች ህዝብን በታማኝነት እና በስነ ምግባር እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።
የመዲናዋ ነዋሪ ሰላም ወጥቶ እንዲገባ እና የከተማዋ ደህንነት እንዲጠበቅ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በሚገባ እንዲወጡ አደራ ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ በበኩላቸው፥ አዲስ አበባ በከፍተኛ ለውጥ እንደምትገኝ እና የኮሪደር ልማቱ መዲናዋ ለአፍሪካ እና ዓለም ተምሳሌት እንድትሆን ቁልፍ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የከተማውንና ለውጥ በሚመጥን ሁኔታ የደንብ ጥሰትን የመከላከል እና የመቆጣጠር ስራን ለማሳለጥ የሚያስችሉ ስራዎችን እየተከናወኑ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ዛሬ የተመረቁ ፓራሚለተሪ ኦፊሰሮች የደንብ ማስከበር ስራን ለማጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ኦፊሰሮች ህገወጥ የደንብ ጥሰትን የመቆጣጠር እና የመከላከል ኃላፊነታቸውን በሚገባ እንዲወጡ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል እና የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መስፍን አበበ፥ ዩኒቨርሲቲው የአዲስ ከተማ አስተዳደር አስተማማኝ የፀጥታ ኃይል ለመገንባት የያዘውን ግብ እየደገፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል።።
ዩኒቨርሲቲው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ የማስከበር ባለስልጣን ጋር በመተባበር ላለፉት ሁለት ዓመታት ለደንብ ማስከበር ኦፊሰሮች ስልጠና እየሰጠ መሆኑን አመልክተዋል።
የስድስተኛ ዙር ሰልጣኞች የንድፈ ሀሳብ እና ተግባር በመውሰድ አስፈላጊውን ብቃትና መመዘኛ ማሟላታቸውን ተናግረዋል።
ኦፊሰሮች ባገኙት እውቀት እና አቅም ህዝባቸውን በታማኝነት እና በስነ ምግባር እንዲያገለግሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ ከተማዋ ያለችበት ደረጃን የሚመጥን የደንብ ማስከበር ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለስልጣን የመዲናዋን ሰላም እና ደህንነት እንዲጠበቅ የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የደንብ አስከባሪ ኦፊሰሮች ህገ ወጥ የመሬት ወረራ በመከላከል፣ ህገ ወጥ ግንባታን በመቀነስ እና ሌሎች ህገ ወጥ ተግባራትን በመመከት ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው ብለዋል።
ተመራቂ ኦፊሰሮች ባገኙት እውቀት እና የተግባር ስልጠና ውስብስብ እየሆነ የመጣውን ህገ ወጥ የደንብ ጥሰትን እንዲከላከሉ እና በኮሪደር ልማት የተሰሩ መሰረተ ልማቶችን በንቃት እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል።