የቢሾፍቱ ከተማ የኮሪደር ልማት የከተማዋን ‘ስማርት ሲቲ' ጽንሰ ሀሳብ እውን በሚያደርግ መልኩ እየተከናወነ ነው

ቢሾፍቱ፤ግንቦት 30/2017(ኢዜአ)፦የቢሾፍቱ ከተማ የኮሪደር ልማት የከተማዋን ‘ስማርት ሲቲ'ጽንሰ ሀሳብ እውን በሚያደርግ እና የቱሪስት ማዕከልነትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን የከተማው ማዘጋጃ ቤት አስታወቀ።

የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ባለፈው ዓመት በሪጂኦፖሊታንት ደረጃ መዋቀሯ የሚታወስ ሲሆን የኮሪደር ልማት ስራም በተሻለ መልኩ እየተከናወነባቸው ካሉ ከተሞች መካከል መሆኗ ተጠቅሷል።

የከተማ አስተዳደሩ ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ገብሬ ዳቢ ለኢዜአ እንዳሉት፥ የከተማው የኮሪደር ልማት ስራ በልዩ ኢኒሺዬቲቭ እየተከናወነ ይገኛል።

የከተማ አስተዳደሩ ስራውን ከመጀመሩ በፊት ለአመራሩ፣ለነዋሪው እና ለባለድርሻ አካላት በልማት ስራው ዙሪያ በቂ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ተከናውኖ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።

ለኮሪደር ልማቱ የግለሰብ፣የመንግስትና የንግድ ቤቶችን ከማፍረስ ባለፈ የመብራት፣ የቴሌኮምና የውኃ መስመሮችን በጥንቃቄ የማንሳት ስራው በተቀናጀ አግባብ ሲከናወን መቆየቱን ገልጸዋል።

የኮሪደር ልማቱ በውስጡ የ24 ኪሎ ሜትር የአስፈልት መንገድ፣ ዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃ ቦዮች፣ የመንገድ ዳርቻ ማስዋብና የአረንጓዴ ስፍራዎች፣ የሳይክልና እና የእግረኛ መንገድን ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም የመብራት፣የቴሌኮም እና የደህንነት ካሜራ በዘመናዊ መንገድ ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተጣጥመው እንዲዘረጉ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

የቢሾፍቱ ከተማ የኮሪደር ልማት ስራ በዋናነት የከተማዋን ‘ስማርት ሲቲ’ ጽንሰ ሀሳብ እውን በሚያደርግ እና የቱሪስት ማዕከልነትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሚከናወን በመሆኑ ስራውም በዚሁ አግባብ እየተፋጠነ ይገኛል ብለዋል።

ቢሾፍቱ በተፈጥሮ የታደለችና የሰባት ሀይቆች ባለቤት መሆኗን አስታውሰ፥ የኮሪደር ልማት ስራው ከተማዋ በተፈጥሮ በታደለችው መስህብ ላይ ተጨማሪ ውበት በሚጨምር መልኩ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

አፈጻጸሙም በታቀደው መሰረት እየተከናወነ መሆኑን ያነሱት ስራ አስኪያጁ የከተማው ነዋሪ፣ባለሀብቶችና ባለድርሻ አካላት ሰፊ ተሳትፎ ማድረጋቸውን አክለዋል።

የከተማው የኮሪደር ልማት ስራ በአማካሪነት የሚከታተለው ድርጅት ምክትል ተጠሪ መሀንዲስ ክበበ በየነ፣ በእስካሁኑ ሂደት የኮሪደር ልማት ስራው 65 በመቶ መከናወኑን አስረድተዋል።

ከአስፋልት መንገድ ባሻገር አምስት ሜትር የእግረኛ፣ ሶስት ሜትር የሳይክል መንገድ፣ በመሬት ውስጥ የሚዘረጋ የኤሌክትሪክ መስመር እና 'ስማርት ፖል' ያካተተ የኮሪደር ልማት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በከተማው ዳካ ቦራ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ ገቢ ዋሪዮ፣ ''በኮሪደር ልማቱ መንገድ እንዲሰፋ እየተደረገ ነው፣ ከተማው እየታደሰ በመሆኑ ስራውን እየደገፍን ነው'' ብለዋል።

በተለይም እየተገነቡ የሚገኙ የአረንጓዴ ስፍራዎች ነዋሪው ንጹህ አየር የሚያገኝበት እና ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮችን የሚፈጽምበት በመሆኑ ስራው ትልቅ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኮሪደር ልማቱ ተጨማሪ የአስፋልት መንገድን ጨምሮ የእግርኛ መንገዶች እየተገነቡ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በከተማው የዱከም ክፍለ ከተማ ነዋሪው አቶ ሚኒሻ ደጀኔ ናቸው።

የኮሪደር ልማት ስራው እንዲፋጠን አስፈለጊውን ድጋፍ ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

ተማሪ ሴና ካሳሁን በበኩሏ፥ በኮሪደር ልማት ሰራው ምክንያት የተሰራው መለስተኛ ፓርክ ለነዋሪው ማረፊያ መሆኑን ጠቅሳ፥ የአካባቢውን ውበትም እየጨመረ መምጣቱን ተናግራለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም