የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ ብሄራዊ ጥቅሟን ከማረጋገጥና ከመጠበቅ አኳያ የሚታይ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 29/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ትከተለው የነበረውን የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ በፖሊሲ ደረጃ በመለወጥና ከብሄራዊ ጥቅሟ አኳያ በመቃኘት እጅግ የተሻለና ያደገ የዲፕሎማሲ አካሄድ መከተሏን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ጋር ባደረጉት ልዩ ቆይታ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲን በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የዓለምን ሁኔታ የተረዳ የነቃና ገለልተኛ፣ ከየአህጉራቱ ወዳጅን የሚያበራክት፣ ችግርንና ደስታን የሚጋሩ ሁነኛ ወዳጆችን እንደሀገር እና መንግስት ማፍራት ያስቻለ አካሄድ እየተከተለች ነው ብለዋል፡፡

ለዚህም ገቢረ ነቢብ የዲፕሎማሲ አካሄድንና ከርእዮተ አለም እስረኝነት የተላቀቀ ዲፕሎማሲ እንከተላለን ነው ያሉት፡፡

የዲፕሎማሲ አጀንዳን በተመለከተ ኢትዮጵያ ከአጀንዳ ተቀባይነት ወጥታ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አጀንዳ ሰጪ መሆን አለባት ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያ የምትፈልገውን ጉዳይ በቅጡ የምታስረዳ ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የምንሽኮረመምበት ሁኔታ የለም ብለዋል።

ዲፕሎማሲያችን ወዳጅን የለየ፣ ስትራቴጂክ አጋርነትን የሚያጠናክር ሆኖ በንግግር ብቻ ሳይሆን በመፈራረም፣ በከፍታም በዝቅታም አብረውን የሚቆሙ ወዳጆች አፍርተናል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ በብዙ መድረክ ለሸምጋይነትና በዓለም አቀፍ ጉዳይ የምትፈለግ ሀገር መሆኗን ጠቁመው የብሪክስ አባል የሆነችው የኢትዮጵያን አስፈላጊነት ማስረዳት በመቻላችን ነው ብለዋል፡፡

በሁሉም አህጉራት የልብ ወዳጆች በማፍራታችንም በመረጃ ልውውጥ፣ በስልጠናና በትጥቅ የሚደግፉን አሉ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው፡፡

ባለፉት ሰባት አመታት እጅግ የተሻለና ያደገ ዲፕሎማሲ አሳክተናል ዲፕሎማሲው ብሄራዊ ጥቅማችንን እያረጋገጥን እንድንሄድ አስችሏል ብለዋል።

በዚህም ከመካከለኛው ምስራቅ፣ ከአውሮፓ፣ ከሩቅ ምስራቅ፣ ከሰሜን አሜሪካ ጠንካራና የምናምናቸው ወዳጆች አፍርተናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ያፈራናቸውን ወዳጆች ዘላቂ ለማድረግ ልመናንና ዕዳን መቀነስና የኤክስፖርት አቅማችንን ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተው አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም