ያልተደመረ አቅም ሀብትና እውቀት የምናስበውን ብልጽግና አያረጋግጥም - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ያልተደመረ አቅም ሀብትና እውቀት የምናስበውን ብልጽግና አያረጋግጥም - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 29/2017(ኢዜአ)፦ ያልተደመረ አቅም ሀብትና እውቀት የምናስበውን ብልጽግና አያረጋግጥም ሲሉ ጠቅለይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ጋር ባደረጉት ልዩ ቆይታ በኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢ የተወሰደውን የእይታ ለውጥ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም አንዱ የዕይታ ለውጥ የመጣው የኢትዮጵያን ሰው፣ መሬት እና ዕውቀት ከጫፍ ጫፍ መጠቀም አለብን መደመር አለብን የሚለው እንደሚገኝበት ገልጸዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢ ያለውን የሰው፣ የመሬት እና የውሃ ሀብት ለልማት ግብዓት እንዲሆን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንና ይህም የመደመር ዋነኛው እሳቤ መሆኑን ተናግረዋል።
የቆላ ልማት ሀገሪቱን የማወቅ ሀብታችንን የማወቅ አቅማችንን የማወቅ እና የመጠቀም ፍላጎታችን አካል ነው ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የሀገሪቱን ሀብት በወጉ ሳናውቅ አቅማችንን ሳናውቅ ያንን አሰናስለን መደመር ሳንችል የምናስበውን ብልጽግና ማረጋገጥ አንችልም ነው ያሉት።
ደቡብ ኦሞን በማሳያነት የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ያለውን የውሃ እና የመሬት ሀብት ከግምት በማስገባት 145 ኪሎ ሜትር ትልልቅ ካናል መሰራቱን ገልጸዋል።
ይህን ማሽን በመጠቀም ማልማት ከተቻለ በምግብ ራስን ለመቻል እና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በምናደርገው ጥረት ውስጥ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በተመሳሳይም በሶማሌ፣ በአፋር እና በኦሮሚያ ክልል ቦረና አካባቢ ተመሳሳይ ሀብት ያለባቸው መሆናቸውን ጠቁመው ቆላ አካባቢ ሰፊ የመሬት ሀብት የሚገኝበት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
ቆላ አካባቢዎች በተፈጥሯዊ የመሬት አቀማመጣቸው ምክንያት የመሬት እና የውሃ ሀብት ያለበት በማሽን ለመጠቀም አስቻይ ሁኔታ ያለበት መሆኑንም ጠቁመዋል።
በመሆኑም እነዚህን አካባቢዎች ሳናለማ የምግብ ሉዓላዊነትም ሆነ ብልጽግና በተሟላ መንገድ ሊመጣ አይችልም ነው ያሉት።