የፕሬዝዳንት ናታሻ ፒሪክ ሙሳር(ዶ/ር) የኢትዮጵያ ቆይታ የሀገራቱን ዲፕሎማሲያዊ ትብብር ወደላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፕሬዝዳንት ናታሻ ፒሪክ ሙሳር(ዶ/ር) የኢትዮጵያ ቆይታ የሀገራቱን ዲፕሎማሲያዊ ትብብር ወደላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው

አዲስ አበባ፤ግንቦት 29/2017(ኢዜአ)፦ የስሎቬንያ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ናታሻ ፒሪክ ሙሳር(ዶ/ር) የኢትዮጵያ ቆይታ የሀገራቱን የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲያዊ ትብብር ወደላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓና አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር አብርሃም መንግስቱ ገለጹ።
የስሎቬንያ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ናታሻ ፒሪክ ሙሳር(ዶ/ር) በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።
ፕሬዝዳንቷ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱም የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተገኝተው ሽኝት አድርገውላቸዋል።
የፕሬዝዳንት ናታሻ ፒሪክ ሙሳር(ዶ/ር) የኢትዮጵያ ቆይታን አስመልከቶ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓና አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር አብርሃም መንግስቱ ለኢዜአ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የስሎቬንያ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ናታሻ ፒሪክ ሙሳር በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት በዓድዋ ድል መታሰቢያ የአበባ ጉንጉን በማስቀመጥ ጭምር ስኬታማ ቆይታ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በቆይታቸውም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ የሀገራቱን ሁለንተናዊ የዲፕሎማሲ ትብብር የሚያጠናክር ምክክር አድርገዋል ብለዋል።
ከፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ጋር በነበራቸው ቆይታም በዓለም አቀፍ ጉዳዮችና በኢትዮ-ስሎቬንያ የትብብር መስኮች ላይ ገንቢ ምክክር ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንቷ የጎዳና ተዳዳሪ የነበሩ ታዳጊዎች በሚማሩበት የዶንቦስኮ ትምህርት ቤት ባደረጉት ጉብኝትም በትምህርት መስክ የሚያደርጉትን ድጋፍ የሚያስቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ በነበራቸው ጉብኝትም ከከንቲባ አዳነች አቤቤ ጋር በመሆን ዘመናዊ የንብ ማነብ ሰርቶ ማሳያ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብርን ማስጀመራቸውንና ስሎቬንያ በከተማ ንብ ማነብ ያላትን ከፍተኛ ተሞክሮ ለማጋራት ያላት ፍላጎትና ዝግጅት የተገለጸበት ነው።
በአጠቃላይ ፕሬዝዳንት ናታሻ ፒሪክ ሙሳር የኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ሁለቱን ሀገራት በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስና በኅዋ ሳይንስ፣ በንብ ማነብ፣ ጥናትና ምርምርን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች በትብብር ለመስራት ከስምምነት መደረሱንም አንስተዋል።
የፕሬዝዳንቷ የኢትዮጵያ ጉብኝትም የሀገራቱን የዲፕሎማሲ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ተቀራርቦ በመስራት ለጋራ ጥቅም በጋራ መስራት የሚቻልበትን ዕድል የፈጠረ ውጤታማ ቆይታ ማድረጋቸውን አስረድተዋል።
ስሎቬንያ ከአንድ ዓመት በፊት ኤምባሲዋን በኢትዮጵያ መክፈቷን የጠቀሱት አምባሳደር አብርሃም፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህም የስሎቬንያ መንግስት የስራ ኃላፊዎች በኢትዮጵያ የሚያደርጉት የስራ ጉብኝት የሀገራቱን የጋራ ተጠቃሚነት እንደሚያሳድግም ተናግረዋል።
የፕሬዚዳንቷ ጉብኝት ንግድና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች የሁለትዮሽ ትብብርን ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው ተገልጿል።