የአብሮነትና የመረዳዳት በዓል የሆነውን ኢድ አል አድሃ (አረፋ) ከአቅመ ደካሞችና ጎረቤቶቻችን ጋር እያከበርን ነው -የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች - ኢዜአ አማርኛ
የአብሮነትና የመረዳዳት በዓል የሆነውን ኢድ አል አድሃ (አረፋ) ከአቅመ ደካሞችና ጎረቤቶቻችን ጋር እያከበርን ነው -የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች
አዲስ አበባ፤ግንቦት 29/2017 (ኢዜአ):- የአብሮነትና የመረዳዳት በዓል የሆነውን ኢድ አል አድሃ (አረፋ) ከአቅመ ደካሞችና ጎረቤቶቻቸው ጋር በጋራ እያከበሩ መሆናቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ተናገሩ
1 ሺህ 446ኛው የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በዛሬው እለት በመላው ኢትዮጵያ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት(ኢዜአ) የአረፋ በዓልን በስግደትና በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓቶች በተከበረበት የአዲስ አበበ ስቴዲዮም ተገኝቶ የበዓሉን አከባበር በተመለከተ ከእምነቱ ተከታዮች ጋር ቆይታ አድርጓል።
በዚህም አስተያየታቸውን ከሰጡት ታዳሚዎች መካከል ሼህ ሳሒል ሐሰን ኢብራሒም እንዳሉት፤ ለአቅመ ደካሞች አለኝታነታችንን በገቢር የምናሳይበት በዓል ነው ብለዋል።
ኢድ አል አድሃ (አረፋ) አቅም በሚፈቅደው ልክ ለአቅመ ደካሞች ማዕድ ማካፈል እንደሚገባ ገልጸው፤ በመሆኑም በዓሉን በመረዳዳት እሴት ከአቅመ ደካሞችና ጎረቤቶቻችን ጋር በአብሮነት በማክበር እንደሚያሳልፉ ተናግረዋል፡፡
ወጣት ከድር አህመድ በበኩሉ መረዳዳት የኢትዮጵያውያን ትልቅ እሴት መሆኑን ጠቅሶ፤ ዛሬ የአረፋ በዓልንም ያልምንም ልዩነት በመተባበርና በመተጋገዝ እያሳለፉ መሆኑን ጠቅሷል፡
የዘንድሮውን በዓል እንደከዚህ በፊቱ ከጎረቤቶቹና ከአቅመ ደካሞች ጋር እያከበረ መሆኑን የተናገረው ደግሞ አብዱል ከሪም ሱልጣን ነው፡፡