ቀጥታ፡

የስሎቬንያ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ናታሻ ፒሪክ ሙሳር በኢትዮጵያ የነበራቸውን ይፋዊ የስራ ጉብኝት አጠናቀው ወደሀገራቸው ተመለሱ

አዲስ አበባ፤ግንቦት 29/2017 (ኢዜአ):- የስሎቬንያ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ናታሻ ፒሪክ ሙሳር በኢትዮጵያ የነበራቸውን ይፋዊ የስራ ጉብኝት አጠናቀው ወደሀገራቸው ተመልሰዋል።

ፕሬዝዳንቷ ወደሀገራቸው ሲመለሱም የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተገኝተው የሽኝት መርሃ ግብር አድርገውላቸዋል።

ፕሬዝዳንት ናታሻ ፒሪክ ሙሳር በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ጋር የሁለቱን ሀገራት የዲፕሎማሲ ትብብር በማጠናከር በጋራ መስራት በሚቻልባቸው ዘርፎች ላይ መምከራቸው ይታወቃል።

ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ከፕሬዝዳንት ናታሻ ፒሪክ ሙሳር ጋር በብሔራዊ ቤተ-መንግስት በነበራቸው ውይይት ኢትዮጵያና ስሎቬንያ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስና በኅዋ ሳይንስ በትብብር ለመስራት ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል።

ፕሬዚዳንቷ በዓድዋ ድል መታሰቢያ የአበባ ጉንጉን በማስቀመጥ፤ ከአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጋር በመሆንም ዘመናዊ የንብ ማነብ ሰርቶ ማሳያ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ማካሄዳቸው ይታወቃል።

እንዲሁም በኢትዮጵያ የነበራቸው ይፋዊ የስራ ቆይታ ንግድና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች የሁለትዮሽ ትብብርን ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው ተገልጿል።

#Ethiopian_News_Agency

#ኢዜአ

#Ethiopia

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም