የዒድ አል አድሀ (አረፋ) በዓል የአንድነትና የአብሮነት እሴቶች በጉልህ የሚንጸባረቁበት በዓል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዒድ አል አድሀ (አረፋ) በዓል የአንድነትና የአብሮነት እሴቶች በጉልህ የሚንጸባረቁበት በዓል ነው
አዳማ፤ግንቦት 29/2017 (ኢዜአ)፦የዒድ አል አድሀ (አረፋ) በዓል የአንድነትና የአብሮነት እሴቶች በጉልህ የሚንጸባረቁበት በዓል ሊሆን እንደሚገባ በአዳማ ከተማ የእስልምና ሀይማኖት አባቶችና ምእመናን ገለጹ።
1 ሺህ 446 ኛው የኢድ አል አድሀ (ዐረፋ) በዓል በአዳማ ኡመር ኢድ መስጅድ የመስጅዱ ኢማሞች፣ ኡላማዎች፣ ሼኾችና ምእመናን በተገኙበት በሃይማኖታዊ ክዋኔዎች በድምቀት ተከብሯል።
የአዳማ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት አባል ሼህ ሁሴን አህመድ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፥ የኢድ አል አድሀ (አረፋ) በዓል በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ትርጉም ያለው፥ የአንድነትና የአብሮነት እሴቶች በጉልህ የሚንጸባረቁበት በዓል መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ በዐረፋ የእምነቱ ተከታዮች ከሚያከናውኑትን እርድ አንድ ሦስተኛውን ለምስኪኖች መስጠት ይገባል ብለዋል።
የአረፋ በዓልን ስናከብር ሁሉም የሙስሊም ማህበረሰብ የሰላም፣የፍቅርና የመተሳሰብ እሴትን በማጎልበትና እውቀትና ጉልበቱን ለመልካም ተግባር በማዋል መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ከበዓሉ ተዳሚዎች መካከል የበዓሉ ታዳሚና የሀይማኖት መሪ ኡስታዝ መስኡድ ኑራ እንዳሉት፥ በበዓሉ ለሌለው እርድ የሚካፈልበት መሆኑን ተናግረዋል።
የኢድ አል አደሀ (አረፋ) በዓል ህዝበ ሙስሊሙ ከሌላው ጋር በፍቅር በአንድነት ተሳስቦ የሚውልበት በዓል መሆኑን አመላክተዋል።
አብዱልጀዋድ አህመድ በበኩላቸው፥ የአረፋ በዓል የእርድ ሥነ ሥርዓት ከመከናወኑ ባሻገር፣ ያለው ከሌለው ጋር ተካፍሎ የሚበላበት፣ መተዛዘንን፣ አብሮነትንና መረዳዳት የሚታይበት በዓል መሆኑን ተናግረዋል።
በዓሉን ስናከብር ፈጣሪ የሚወደውን በጎ ተግባር በመፈጸም፣ የተቸገሩትን፣ የታመሙትንና አቅመ ደካሞችን በማሰብ ሊሆን ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።