ኢትዮጵያና ስሎቪኒያ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስና ህዋ ሳይንስ በትብብር እንደሚሰሩ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ስሎቪኒያ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስና ህዋ ሳይንስ በትብብር እንደሚሰሩ ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 28/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያና ስሎቪኒያ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስና በህዋ ሳይንስ በትብብር እንደሚሰሩ ገለጹ።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የስሎቪኒያ ፕሬዚዳንት ናታሻ ፒርክ ሙሳርን በብሔራዊ ቤተመንግስት ተቀብለው አነጋግረዋል።
ፕሬዚዳንት ታዬ ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ ከስሎቪኒያ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ጋር በዓለም አቀፍና የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ገልጸዋል።
ስሎቪኒያ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል በመሆኗ በቆይታዋ፣ ምክር ቤቱ የአፍሪካ ጉዳዮችን በሚያይበት ወቅት ማገዝ በምትችልባቸው ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን ገልጸዋል።
አፍሪካን በሚመለከት ሚዛናዊ እይታ ያላቸው፣ የአፍሪካ ድምጽ በመታበይ ስሜት ሳይሆን እኩልነትና ሚዛናዊነትን የሚፈልጉ እንደሆኑ መረዳታቸውን አንስተዋል።
የጸጥታው ምክር ቤት በጂኦ-ፖለቲካልና ጂኦ-ኢኮኖሚክ መስፈርቶችና የአገራት ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል በማድረግ ሪፎርም ለማድረግ መሰራት ባለባቸው ጉዳዮች ዙሪያም መወያየታቸውን ተናግረዋል።
ዓለም አቀፍ ውጥረት የባለብዙወገን ሃሳብና ዲፕሎማሲ ፈተና ውስጥ ከወደቀባቸው ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ እንደሆነ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ጠቁመዋል።
ጥቂት ሀገራት በአለም ህልውና ላይ ሊወስኑ እንደማይገባ በመግለጽ በመካከለኛ ሃይል ሊፈረጁ የሚችሉ ሀገራት ሊኖራቸው በሚችለው ድምጽ ላይ መክረናል ብለዋል።
በሁለትዮሽ ጉዳዮች ስሎቪኒያ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስና በስፔስ ሳይንስ ያላትን የዳበረ አቅም በማሸጋገር ዙሪያ በጋራ ለመስራት በአጽእኖት መወያየታቸውን ገልጸዋል።
በምግብ ራስን ለመቻል በከተማ ግብርና በንብ ማነብ ያላቸውን ልምድ በማካፈል በትብብር እንደሚሰሩም አብራርተዋል።
የስሎቪኒያ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ናታሻ ፒርክ ሙሳር በበኩላቸው፤ ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ጋር በሁለትዮሽ፣ በአለም አቀፍና የባለብዙ ወገን ግንኙነት ላይ ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ስሎቪኒያ ሙሉ ድጋፍ እንደምታደርግም ገልጸዋል።
ከኢትዮጵያ ጋር በምጣኔ ሃብት፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ የውሃ አስተዳደርና በሌሎች ዘርፎች በትብብር መስራት የሚፈልጉባቸው እንደሆኑ ገልጸዋል።